post-thumb

ቨርቹዋል ኦቲዝም

የብዙ ወላጆች ዓለም ልጆቻቸው ናቸው። ወላጆች ልጆቻቸው ጤነኛ ሆነው እንዲያድጉ እና የነገ ህይወታቸው ያማረ እንዲሆን ሲሉ ብዙ መስዋትነትን ይከፍላሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ልጆቻቸው በሚታመሙባቸው ጊዜ ወላጆች የሚገቡበት ጭንቀት እና ፈተና በቃላት የሚገለጽ አይደለም።


በተለይም ደግሞ ልጆቻቸውን ያጋጠማቸው የአዕምሮ ጤና ችግር ከሆነ ጉዳዩን ይበልጥ አስጨናቂ እና ውስብስብ ያደርግባቸዋል። ውስብስብ ከሚደርጉባቸውም ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ወላጆች ዘንድ ስለልጆች የአዕምሮ ጤና ያለው እውቀት እና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ ነው። በዚህ ግንዛቤ ማነስ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ወላጆች ከሚፈተኑባቸው እና የልጆችን የአዕምሮ ጤናም ከሚጎዱ ህመሞች መካከል "የኦቲዝም ህመም" ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።


በሀገራችን ኢትዮጵያ በኦቲዝም ህመም ዙሪያ ያለው የግንዛቤ ማነስ በወላጆች ብቻ የሚስተዋል አይደለም ፤ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍልም ስለ ኦቲዝም ህመም በቂ ግንዛቤ ና እውቀቱ የለውም። የኦቲዝም ህመም ጆሮ እንኳን በቅጡ ያልሰጠነው ግን ደግሞ ለብዙዎቻችንን ጓዳ ቅርብ እየሆነ ያለ አሳሳቢ የጋራ ጉዳያችን ነው።


በዚኅ ጹሑፋችን ለመዳሰስ የምንሞክረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከልጆች የስክሪን አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ይፈጠራል ስለተባለውና በርካታ ወላጆችም ስለሚጨነቁበት በስፋት ‹ቨርቹዋል ኦቲዝም›› የሚል ስያሜ ስለተሰጠው ‹‹ኦቲዝም መሰል›› የጤና እክል ላይ ይሆናል፡፡


ለዚሀም መነሻ የሆነን መደበኛ በሚባለው የኦቲዝም ህመም ላይ ያለው መረዳት በሁለት ጽንፍ ያለ፤ አንዱ ስለ ኦቲዝም ምንም በሚባል መልኩ አነስተኛ ግንዛቤ መኖሩ፤ ሌላኛው ደግሞ ከፍርኃትና ከተለያዩ አመለካከቶች፤ እጅግም በጣም አስፈሪና የፈጣሪ ቁጣ አስመስሎ ከማየት የተነሳ ኦቲዝምን በቅጡ ካለመረዳት የተዛቡ ምልከታዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ከልጆች አስተዳደግና ከስክሪን አጠቃቀም የተነሳ የሚስተዋለውንና ለብዙ ወላጆች ጭንቀት እየሆነ ስለመጣው "ቨርቹዋል ኦቲዝም" ምንነትን ፣ ባህሪ እና ተጽዕኖ ከመደበኛው ኦቲዝም ጋር በንጽጽር የሚዳስስ ይሆናል፡፡

ቨርቹዋል ኦቲዝም ምንድነው? 

ቨርችዋል ኦቲዝም ከ5 ዓመት በታች በተለይም ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ቴሌቭዥን፣ ስልክ እና ታብሌት ላይ ብዙውን ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የሚያሳዩት ኦቲዝም መሰል የጤና እክል ሲሆን የህጻናትን የንግግር ክህሎት ላይ ፣ ማህበራዊ ግንኙነትን እና ባህሪያቸው ላይ እክል የሚያስከትል የጤና ችግር ነው።  

 
ቨርቹዋል ኦቲዝም የሚባለው የጤና ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣ (በተለይም በኮቪድ ጊዜ ይበልጥ መስተዋል የጀመረ) ሲሆን እስኳሁን ድረስ ግን በዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ በ "DSM5 Manual"   ላይ ያልተካተተ እንዲሁም Offically diagnosis ያልተደረገ የጤና እክል ነው።


የአዕምሮ ህመሞች እንደሌላው የህመም አይነቶች የተለያዩ ናሙናዎችን በመውሰድ የሚለዩ ባይሆንም የራሳቸው " DSM " የተባለ Manual Guide አላቸው።


የዘርፉ ባለሙያዎች የትኛውንም የአዕምሮ ህመም የሚመረምሩትም ሆነ ህክምና የሚሰጡት "DSM" የተባለውን መምሪያ መሰረት በማድረግ ነው።


"DSM 5" ምንድነው?

  "DSM"( Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders) በመባል የሚታወቅ የአዕምሮ ሕመሞችን መመርመሪያ እና ስታስቲካዊ ማኑዋል ሲሆን በአዕምሮ ጤና እና ከአዕምሮ ጋር በተያያዙ ለሚፈጠሩ መታወኮች የማመሳከሪያ መጽሐፍ ነው።

Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders
Diagnostic and Statistical Manual of Mental Disorders

ይህ "DSM" የሚባለው ጥራዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው እ.አ.አ በ2013 ላይ ሲሆን በየጊዜው እየተሻሻለ እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ የሥነ-አዕምሮ ማኅበር እየታተመ "DSM -5 TR" የተሰኘውና አምስተኛው ዕትም ላይ ደርሷል። 
በ "DSM 5 TR" ላይ ኦቲዝምን ጨምሮ ከ70 በላይ የአዕምሮ ህመሞች በውስጡ የተካተቱ ሲሆን ቨርችዋል ኦቲዝም ግን በእዚህ እትም ውስጥ አልተካተተም። ሆኖም ቨርቹዋል ኦቲዝምን ከሚያሳየው ምልክት እና ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር  ባለሙያዎች ትንታኔ እና ህክምና ይሰጡበታል።


ቨርቹዋል ኦቲዝም ከባለሙያዎች አንጻር እንዴት ይገለጻል?

ቨርቹዋል ኦቲዝም ልጆች በተለይም ከ2 አመት በታች የሆኑ ህጻናት  ረጅም ሰዓት ያለገደብ ለተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች ማለትም እንደ ስልክ ፣ ቴሌቭዥን ፣ እና ታብሌት ላይ ተጋላጭ ሲሆኑ የሚያሳዩት ኦቲዝም መሰል የጤና እክል ነው በማለት ባለሙያዎች ይገልጹታል።


ማህሌት አዘነ የንግግር እና ቋንቋ ቴራፒስት ስትሆን ቨርችዋል ኦቲዝም የታወቀ medical diagnosis እንዳልሆነ እና  የዓለም ጤና ድርጅትም በመደበኛ ምርመራ ውስጥ እንዲካተት እንዳላደረገው ትናገራለች። ነገር ግን ቨርቹዋል ኦቲዝም ባለሙያዎች በሚያዩት ነገሮች በመነሳት ህጻናት ስክሪን ላይ በሚኖራቸው ቆይታ የተነሳ የሚከሰት ነው ተብሎ እንደሚታሰብ እና የኦቲዝም ምልክቶችን የሚያሳይ የጤና እክል መሆኑንንም ትገልጻለች።

ማህሌት አዘነ - የንግግር እና ቋንቋ ቴራፒስት
ማህሌት አዘነ - የንግግር እና ቋንቋ ቴራፒስት

"ህጻናት እስከ ሁለት ዓመታቸው ቴሌቭዥንም ሆነ ስልክ ማየት የለባቸውም" የምትለው ማህሌት " ይህ እድሜያቸው ከሰው ጋር መግባቢያ ሆኖ ሳለ ልጆቹ ግን ቴሌቭዥን እና ስልክ ላይ በሚያሳልፉበት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ችግር ነው ቨርችዋል ኦቲዝም ተብሎ የተሰየመው፤ ነገር ግን የአለም ጤና ድርጅት እንደ መደበኛው ኦቲዝም formally diagnosis ያደረገው ነገር አይደለም" በማለት ታስረዳለች።

ህጻናት እስከ ሁለት ዓመታቸው ቴሌቭዥንም ሆነ ስልክ ማየት የለባቸውም


በቅርቡ ‹‹የኦቲዝም ሚስጥሮች›› የሚል መጽሐፍ ለህዝብ ያደረሰችው እና የህጻናት ህክምና ስፔሻሊስት የሆነችው ዶ/ር ሀድያ ተማም በኦቲዝም ዙሪያ ካላት እውቀትና ልምድ በመነሳት ቨርችዋል ኦቲዝምን አስመልክቶ ማብራሪያ ጠይቀናታል፡፡

‹የኦቲዝም ሚስጥሮች›› - ዶ/ር ሀድያ ተማም
‹‹የኦቲዝም ሚስጥሮች››  ዶ/ር ሀድያ ተማም

 

ዶ/ር ሀዲያ ተማም ቨርችዋል ኦቲዝም የሚባል ምድብ በራሱ እንደሌለው ታስረዳለች፡፡ "DSM -5 TR የሚባል አለ አሁን በቅርቡ የወጣ እዛ ላይ ራሱ ስለ ኦቲዝም ፡ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር (ASD) ብሎ ነው ያስቀመጠው። በፊት ራሱ "ASD" የሚባለው ብዙ Classification ነበረው ፤ ወደ 5 የሚሆኑ classfications ግን አሁን እንደ አጠቃላይ ሁኖ "DSM-5 TR" የሚባለው classification ሁሉን በአንድ ላይ አካቶ "ASD" ብሎ ነው የጻፋቸው: እዛ ላይ ቨርችዋል ኦቲዝም የሚባል classification የለም።"ስትል ትገልጻለች፡፡


ሆኖም ግን ምንም እንኳን ቨርችዋል ኦቲዝም በህክምናው የተሰጠው ምድብ ባይኖርም ምልክቶች ተብለው የሚጠቀሱት ግን እንደሚስተዋሉ ያስረዳሉ "ቨርችዋል ኦቲዝም የሚባለው ልጆች ለቲቪ ፣ ለሞባይል ፣ ለስክሪን በጣም ሲጋለጡ በተለይ ከ2 አመታቸው በታች ለዛ ተጋላጭ ከሆኑ ኦቲዚም መሰል ምልክቶችን ያሳያሉ። ያም ምንድነው ቶሎ አፍ አለመፍታት ፣ ቁጡ መሆን ፣ ትዕዛዝ ሲታዘዙ አለመታዘዝ ፣ ስልክ ሲቀሙ በጣም መረበሽ እናም ሌሎች የስሜት ለውጦች ያሳያሉ ይሄንን ነው ቨርቹዋል ኦቲዝም የምንለው" በማለት ታስደዳለች፡፡


የቨርቹዋል ኦቲዝም እና የመደበኛው ኦቲዝም ልዩነት እና አንድነት ?

አንድነት

በጣም ተመሳሳይ ምልክቶች ወይም ባህሪያት አሏቸው 
ሁለቱም የህጻናት የንግግር ክህሎት ላይ ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እና  ባህሪያቸው ላይ እክል ይፈጥራሉ
ሁለቱም የባለሙያ ክትትል እና ህክምና ይፈልጋሉ

ልዩነት

ቨርቹዋል ኦቲዝም መምጫ ምክንያቱ በውል የሚታወቅ እና ህጻናት ከውልደት በኋላ ከስክሪን ጋር በሚኖራቸው ተጋላጭነት የሚከሰት ሲሆን
ኦቲዝም በአንጻሩ መነሻ ምክንያቱ በውል የማይታወቅ በውልደት የሚመጣ ዘላቂ የአዕምሮ እድገት እክል ነው
ቨርቹዋል ኦቲዝም የስክሪን ግዜ ሲቀነስ / ሲቆም  እና ተገቢውን ህክምና ካገኘ ከ5-6ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ለውጥ የሚያሳይ ሲሆን
ኦቲዝም ግን ረዘም ያለ ና ውስብስብ ህክምና የሚጠይቅ ዘላቂ የሆነ የጤና እክል ነው

ቨርቹዋል ኦቲዝም እንዴት ይከሰታል ?

ህጻናት አዕምሮዋቸው በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድገው በመጀመሪያዎቹ 3 አመታት ውስጥ ነው። በዚህ ወቅት የህጻናት አዕምሮ ለቴሌቪዥን ፣ ለሞባይል ፣ ታብሌት እና ለሌሎች ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ሲጋለጥ የአዕምሮ እድገታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይመጣል። 


 የዓለም ጤና ድርጅት ከ2 አመት በታች የሆኑ ልጆች ለየትኛውም ስክሪን እንዳይጋለጡ በጥብቅ ይመክራል የምትለው ዶ/ር ሀዲያ ተማም " ይህ የተባለው የአዕምሮ እድገታቸው ላይ ጫና ስለሚፈጥር ነው ፤ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ ንግግር ክህሎታቸው እንዳይዳብር ያደርጋል፣ ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነታቸው እንዳይጎለብት ያደርጋል ፣ የጨዋታ ዝንባሌ እንዳይኖራቸው ያደርጋል" በማለት ትገልጻለች።


የንግግር እና ቋንቋ ቴራፒስቷ ማኅሌት አዘነ በበኩሏ ልጆች በእነዚህ 2/3 አመታት ውስጥ በአግባቡ ማደግ አለባቸው ፤ ከወላጆቻቸው ጋር መጫወት አለባቸው ፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህጻናት በስክሪን ላይ የሚያሳልፉ ከሆነ ይህ የጨዋታ ጊዜያቸው ያልፋቸውና ጉዳጽ ላይ እንደሚወድቁ ታስረዳለች።

"እነዚህ ህጻናት ከልጆች ጋር መጫወት ባለባቸው ሰዓት ለብቻቸው ነው የሚያሳልፉት ፤ ይሄ ደግሞ ብቸኝነት ያስለምዳቸውና ከልጆች ጋር መቀላቀልን እንዲፈሩ ያደረጋቸዋል" በማለት እንዴት ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን እንደሚጎዳ ትገልጻለች፡፡ህጻናት ስለ አከባቢያቸው የሚማሩት ነገሮችን በመንካት ፣ በመዳበስ ፣ በማሽተት ፣ በማየት እና በመቅመስ ነው የሚሉት ዶ/ር ሀዲያ ተማም " ስክሪን ላይ ብዙ ሰዓታት የሚያሳልፉ ህጻናት ግን ይህ እድል ስለማይኖራቸው ከእውነተኛው ዓለም የተነጠሉ ይሆናሉ ፤ በዚህም ምክንያት ኦቲዝም መሰል ምልክቶች ይከሰትባቸዋል፡፡ በመሆኑም በትክክለኛው መንገድ ማደግ ያለበት ልጅ ለኤሌክትሮኒክስ ስክሪን ተጋላጭ በመሆኑ ምክንያት ሌሎች ባህሪያትን እንዲያሳይ ያደርገዋል ፤ ለዚህም ነው የአለም ጤናም ድርጅትም ሆነ እኛ ሀኪሞች የህጻናት ስክሪን ጊዜ እንዲገደብ እና ጥንቃቄ እንዲደረግበት የምንመክረው" ሲሉ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ።


ለቨርቹዋል ኦቲዝም አጋላጭ የሆኑ መንስኤዎች

  • ልጆች ሲያስቸግሩ ዝም እንዲሉ በማለት ቴሌቭዥን መክፈት/ ሞባይል መስጠት
  • ምግብ አልበላ ሲሉ ሞባይል/ ቴሌቭዥን እያሳዩ ማብላት
  • ከሞግዚት ጋር ብቻ ሲውሉ እና ፡ እነሱም ሥራ ለመስራት ሲሉ ቴሌቭዥን ከፍተው ፣ወይም ሞባይል/ ታብሌት ሰጥተው ቀኑን ሙሉ የሚያውሏቸው ከሆነ
  • በተጨማሪም በተለይ 'Cocomelon' የሚባለው የህጻናት ፊልም እጅግ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ብዙ ቀላማት ስላላው እሱን ሲመልከቱ የሚውሉ ህጻናት ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ቨርቹዋል ኦቲዝም ምልክቶች መካከል

የቋንቋ ፣ የንግግር እና የተግባቦት ችግር ይከሰታል 

ማለትም ህጻናት 1ዓመት ላይ እማ ፡ አባባ ይላሉ።   2 አመት ላይ እስከ 50 ቃላት ይችላሉ። በቨርቹዋል ኦቲዝም የተጠቁ ህጻናትን ግን ይህን ማድረግ ያቅታቸዋል ፤ አንዳንዴም የቻሉት ንግግር/ ቋንቋ ራሱ ወደኋላ ሊመለስባቸው ይችላል።

ትኩረት አለማድረግ ፣ ትግስት ማጣት

አንድን ነገር ትኩረት ሰጥቶ መጨረስ ያቅታቸዋል ፤ ማጫወቻ ቢሰጣቸው ትኩረት ሰጥተው ፣ ትግስት ኑሯቸው አይጫወቱም ፤ ትግስት አለባ ይሆናሉ።

ትእዛዝ ሲታዘዙ ትዕዛዝ አለመቀበል

ስማቸውን አይረዱም ፣ ሲጠሩ አይመልሱም ፤ ትዕዛዝም አያከብሩም።

ስሜታቸውን በተለየ መንገድ መግለጽ

ሲደሰቱ እጃቸውን በተደጋጋሚ ማወዛወዝ። 

ከሌሎች ህጻናት ጋር ለመጫወት አለመፈለግ 

ከህጻናት ጋር ተቀላቅሎ ለመጫውት ይፈራሉ ፣ ተግባብተው ለመጫወት አይሞክሩም ፤ ራሳቸውን አግልለው ለብቻቸው ይጫወታሉ።

መቀዥቀዥ ፣ ቅብጥብጥ ማለት እና እረፍት የለሽ መሆን

ፊልም ላይ የሚያይቱን ባህሪ ነው የሚያሳዩት ።
ለምሳሌ ፡ "Cocomelon" የሚባል ፊልም ፣ ሌሎችም ፊልሞች ፈጣን እንቅስቃሴ ስላላቸው ፡ እዛ ላይ ያዩትን ባህሪ ነው የሚያሳዩት  መቀዥቀዥን እና መቅበጥበጥን ያሳያሉ

በቀላሉ መረበሽ ፡ ቁጡ መሆን

ስሜታቸውን መቆጣጠር ስላልተማሩ እና  እንደ ሱሰ ስለሚሆንባቸው ስልክ/ቲቪ ሲነጠቁ ፣ መብራት ሲጠፋባቸው በቀላሉ ስሜታቸው የረበሻል ፣ በጣም ቁጡ ይሆናሉ።

የቨርቹዋል ኦቲዝም ህክምና

  • የስክሪን ግዜን ቀስ በቀስ መገደብ እና ማቆም
  • የሥነ ባህሪ እና የንግግር ህክምናዎች መጀመር
  • ልጆች ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተቀላቅለው እንዲጫውቱ ማድረግ
  • አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማድረግ
  • መጽሀፍት እያነበብንላቸው ታሪኩን እንዲሰሙ ማድረግ ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው   

ቨርቹዋል ኦቲዝም እና የወላጅ እይታ

ቨርቹዋል ኦቲዝምን አቅልሎ ማየት እና መዘናጋት፡-
ወላጆች ልጆቻቸው ቨርቹዋል ኦቲዝም አለበት ሲባሉ ነገሩን አቅልለው ይመለከቱትና ይዘናጋሉ፡፡ ሁሉም ነገር ቴሌቭዥን/ሞባይል በማቆም ብቻ የሚስተካከል ይመስላቸዋል። በዚህም የተነሳ ልጆቹ ተገቢውን ክትትል እና ህክምና ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ የባለሙያዎቹ ምክር ግን ስክሪን ከማስቆም ባሻገር እንደ ልጆቹ ሁኔታ የተለያዩ ህክምናዎች እንደሚያስፈልግ ነው።

ቨርቹዋል ኦቲዝም ህክምና እንደሚያስፈልገው አለማሰብ፡
በዚህ ረገድ ዶ/ር ሀድያ ካጋጠማቸው ተነስተው " ለወላጆች ቨርቹዋል ኦቲዝም ነው ብለሻቸው ፥ ልጁ የንግግር ህክምና አድርጉ ብትያቸው አያደርጉም፤ ከስንት አንድ ነው ህክምናውን የሚያደርገው፡፡ ልጄ ደህና ነው ፤ ቲቪ እና ሞባይል ካቆምኩኝ ደህና ይሆናል ብሎ ስለሚያስቡ ልጆቹ ማግኘት የሚገባቸውን ህክምና አያገኙም ፤ ይሄ ደግሞ የልጆቹን ጤና እና የማገገም እድል በጣም ይጎዳል " በማለት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።     

ቨርቹዋል ኦቲዝም በመደበኛው ኦቲዝም ላይ እያሳደረ ያለው ከፍተኛ ተጽዕኖ

የቨርቹዋል ኦቲዝም ከመደበኛው ኦቲዝም ጋር እጅግ ተመሳሳይ ምልክቶች ስላሉት በምርመራ ጊዜ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ባለሙያዎች አጽኖት ሰጥተው ይመክራሉ።


"በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንድ 'መደበኛ ኦቲዝም' ያለበትን ልጅ 'ቨርቹዋል ኦቲዝም' ነው እየተባለ ምርመራ ይደረጋል ፡ ያ ደግሞ ልክ አይደለም " የሚሉት ዶ/ር ሀዲያ "ለምሳሌ እኛ ጋር ይመጣሉ ቨርቹዋል ኦቲዝም ነው ዲያግኖሲስ የተደረግነው ብለው ፡ እና ሲመጡ ከ6ወር እስከ 1 ዓመት ቲቪ አቁመው ይመጣሉ ፥ ግን ልጆቹ ኦቲዝም መስፈርትን የሚያሟሉ ሁነው ይገኛሉ ፤ ስለዚህ በድጋሚ ዳይግኖሲስ እናደርጋቸዋለን። ስለዚህ ኦቲዝም እና ቨርቹዋል ኦቲዝም ዳይግኖሲስ በሚደረግበት ጊዜ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ፤ አለዚያ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል" በማለት አጽኖት በመስጠት የጥንቃቄ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ


ከወላጅ አንጻር ያለው ተጽዕኖ

ሀ. ወላጆችን መዘናጋት ችግር
ቨርቹዋል ኦቲዝም ከመደበኛው ኦቲዝም ጋር ተመሳሳይ ባህሪዎች ስላሉት ፡ ወላጆች 'መደበኛውን ኦቲዝምን' ልክ እንደ 'ቨርቹዋል ኦቲዝም' በመቁጠር እንደሚዘናጉ ዶ/ር ሀዲያ ተማም ያስረዳሉ፡፡

 "በኦቲዝም ህክምና ላይ በጣም ወሳኝ ሰዓት የሚባለው ከ5 ዓመት በታች ያለው እድሜ ነው ፤ ሩጫው ከእድሜ ጋር ነው። እናም በዚህ መዘናጋት ምክንያት ኦቲዝም የሆኑ ህፃናት በዛ ለጋ እድሜ ማግኘት የሚገባቸውን ህክምና ሳያገኙ ይቀራሉ። ይሄ ደግሞ የልጆቹን የወደፊት ጤና ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል" በማለት የወላጆች መዘናጋት እንዴት ትልቅ ዋጋ እያሳከፈለ እንዳለ ይናገራሉ።


ለ. የወላጆች አምኖ አለመቀበል ፣ ምክንያት መደርደር እና ቨርቹዋል ኦቲዝምን እንደ መከላከያ መጠቀም

አብዛኛው ወላጅ ልጄ ላይ ኦቲዝም አይፈጠረም ብሎ በማሰብ የቨርቹዋል ኦቲዝም መንስኤዎችን ነው እንደ ምክንያት የሚያቀርበው የሚሉት ባለሙያዎቹ "ለሁለቱም ኦቲዝም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ቲቪ እና ስልክ ነው" በማለት ቴራፒስት ማህሌት ጉዳዩን ስታስረዳ፤ ዶ/ር ሀዲያም በበኩላቸው " አንዳንዶቹ ምን ይላሉ ልጄ ኮንደምኒየም ስለሚኖር ነው ፣ ቲቪ ስለሚያይ ነው ፣ ልጄ ከልጆች ጋር ስለማይጫወት ነው ብለው ምክንያት ይደርድራሉ እንጂ ኦቲዝም ነው ብሎ ማመን አይፈልግም" በማለት ወላጆች ዘንድ የተሳሳተ ምልከታ መኖሩን ትገጻለች፡፡


አብዛኛው ወላጅ ቨርችዋል ኦቲዝምን እንደ መከላከያ እየተጠቀመ መሆኑንም የሚናገሩት ዶ/ር ሀዲያ " ወላጅ ስለ ቨርቹዋል ኦቲዝም በየሚዲያው ስለሰማው ያንን እንደ መከላከያ እየተጠቀመው ነው ፤ ወላጅ ኦቲዝም ሲባል ብዙ ጫና ውስጥ ስለሚገባ ከመደበኛው ኦቲዝም ይልቅ ቨርቹዋል ኦቲዝም ቢባል ይመርጣል" በማለት የቨርቹዋል ኦቲዝም ተጽዕኖ ያስረዳሉ።


ቨርቹዋል ኦቲዝምን ለመከላከል የተሰጠ ምክረ ሀሳብ 

1. ለልጆች ኤሌክትሮኒክስ ከመስጠት ይልቅ መጽሀፍትን መስጠት እና ማንበብ (የተረት መጽሀፍ ፣ ስእላዊ መጽሀፍትን)
2. የልጆችን የስክሪን ጊዜን መገደብ እና መከታተል

  • ከ2 አመት በታች የሆኑ ህጻናት ለምንም አይነት ስክሪን መጋለጥ የለባቸውም።
  • ከ2-5 አመታቸው ደግሞ በቀን ከ1 እስከ 2 ሰአት ብቻ እንዲሆን እና እሱንም የተመረጡ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ብቻ እንዲመለከቱ ይመክራል

3. ለልጆች ትኩረት መስጠት

  • ከልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ፣ ማጫወት ፣ መዘመር
  • ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲጫወቱ በመፍቀድ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ መርዳት
  • ከምናባዊ ዓለም ይልቅ ተፈጥሮአዊን አለም እንዲረዱት ማድረግ ለምሳሌ፥ መጫወቻ ቦታዎች መውሰድ 

4. በዋነኝነት ስለ ልጆች የአስተዳደግ ሁኔታ እና የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ ላይ ያለን እውቀት እና ግንዛቤ ማሳደግ
5. ልጆች ላይ አጠራጣሪ ምልክት ካየን ችላ ከማለት እና ልጆችን ቤት ውስጥ ከመደበቅ ይልቅ ባለሙያን ማማከር እንዲሁም ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡



Tinsae Abebe

Freelance writer

የዚህ ጹሑፍ አዘጋጅ ትንሳኤ አበበ በሜድካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ተመርቃለች። አሁን ላይ ሀብ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረት አድርጋ በመስራት ላይ ትገኛለች።

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.