በቁንፅል የምናስተምረው ፓን አፍሪካኒዝም
በመንግስት ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል የታሪክ መምህር የሆነው መልካሙ ላመስግን ኬኒያዊ መምህር ጓደኛው ‹‹የታሪክ መጽሐፋችንን ተመለክቶ የታለ የአፍሪካኒስቶች ታሪክ፣ የታለ የፓን አፍሪካኒዝም ታሪክ በደንብ የተገለፀው›› ብሎ ‹‹እናንተ አውሮፓ ተኮር ለሆኑ ትምህርቶች ታተኩራለችሁ›› ሲል እንደተናገረው ያስታውሳል፡፡
የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው አዝመራው አሂባቸው በበኩሉ ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ታሪክ ትምህርት ላይ በተማረው አዕምሮው ላይ የተቀመጠ ነገር ስላለመኖሩ፤ እንደውም ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ትምህርት ትዝ ያለው ጥያቄው ሲቀርብለት እንደሆነ ይናገራል።
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያ ጨምሮ ስለ ፓን አፍሪካኒዝም በታሪክ ትምህርታቸው ውስጥ በማካተት ተማሪዎቻቸውን ቢያስተምሩም÷ የሚሰጠው ትምህርት መሰጠት በሚገባው ልክ ተሰጥቷል የሚለው ግን ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡

የሩዋንዳ የተማሪዎች መማሪያ ታሪክና ሲትዝንሽፕ መፅሀፍ
የሩዋንዳ የተማሪዎች መማሪያ ታሪክና ሲትዝንሽፕ መፅሀፍ ላይ ፓን-አፍሪካኒዝም በአፍሪካ ውስጥ ባሉ አፍሪካውያን እና በዲያስፖራ አፍሪካውያን የተቋቋመ ድርጅት እንደሆነ፤ በማርከስ ጋርቬይ እና ዱ ቦይስ መቋቋሙን፤ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ሂደቱን ለማፋጠን መጥቀሙን እና 'አፍሪካ ለአፍሪካውያን' የሚለውን እሳቤ መፍጠሩን በ1 አንቀጽ በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል።
በአንጻሩ የኢትዮጵያ 12ተኛ ክፍል ታሪክ መጽሐፍን ብንመለከት ከሩዋንዳው ታሪክ መፅሀፍ በተሻለ በ1 ገፅ ከግማሽ ስለፓን አፍሪካኒዝም ያስተምራል። የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ለመፈጠሩ ዋናው ምክንያት በውጭ የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ከመጡበት አፍሪካ ርቀው ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ራሳቸውን ሀገር አልባ እደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር እንደሆነ ያስረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰቡ እንዲነሳ ትልቅ መንፈሳዊ አቅም የሆነው ኢትዮጵያ በአድዋው ጦርነት ጣሊያንን በማሸነፏ እንደሆነ የኢትዮጵያ 12 ክፍል የታሪክ መፅሀፍ ያመላክታል።
በመጽሐፉ እንደተገለጸውም ሆነ ብዙዎች እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጀመር አንዷ ምልክት ነች፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ ቢኖራትም በታሪክ ትምህርቶቿ ላይ ስለፓን አፍሪካኒዝም በምን ያህል መልኩ ተማሪዎችን እያስተማረች ነው? የሚለው ጥያቄ ግን መነሳት ያለበት ነው፡፡
መምህር መልካሙ ላመስግን ፓን አፍሪካኒዝም በተወሰነ መልኩ በ11ኛ ክፈል የተማሪዎች ማስተማሪያ ታሪክ መጽሐፍ ላይ ስለመኖሩ ይጠቅሳል፡፡ በጥልቀት ግን ፓን አፍሪካኒዝምን አለመዳሰሱን ያነሳል። ‹‹ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ያበረከተችው አስተዋፅኦ በአግባቡ በመማሪያ መጽሐፉ ላይ አልተገለጸም ከዛ ይልቅ አውሮፓ ተኮር ታሪኮች ይበዛሉ›› ሲል ተናግሯል።
አክሎም ‹‹ለፓን አፍሪካኒዝም አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰዎች ታሪክ በአግባቡ መጽሐፍ ላይ አልተገለፀም። መጽሐፍ ላይ ያለው÷ ፓን አፍሪካኒዝም መስራቾች እነማን ናቸው ፤ ፓን አፍሪካኒዝም አባት ማን ነው የሚለውን ይገልጽና በደንብ ሳያብራራ ያቆማል›› ሲል ይስረዳል። የፓን አፍሪካኒዝም መስራቾች ዱ ቦይስና ማርከስ ጋርቬይ በፊት በአሁኗ ሀይቲ የጥቁሮች መብት እንዲከበር ሰዎች አደባባይ ወጠው እንዲቃወሙ ሲመራ የነበረው ቱሰንት ሎወቨር ቸር የመሳሰሉ ሰዎች ታሪክም አለመካተቱን መምህር መልካሙ በታሪክ መማሪያ መጽሐፍቶቻችን በዚህ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው ይጠቅሳል፡፡
በመንግስት ትምህርት ቤት የ11 ክፍል ተማሪ የሆነችው ሃይማኖት ታረቀኝ ‹‹እኔ ክፍል ውስጥ የታሪክ ትምህርት ስማር ፓን አፍሪካኒዝም የት ተጀመረ፣ እነማን ጀመሩት የሚለውን ተምሪያለው። ነገር ግን በደንብ በጥልቀት ስላልሆነ በተማርነው ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ብዙ ግንዛቤው የለኝም›› ስትል ተናግራለች። ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ታሪክ ትምህርት ስማር ከማቀው ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በማያቸው ነገሮች ባገኘውት የተሻለ እውቀት አለኝ ብላለች።
ሌላኛዋ በግል ትምህርት ቤት የ12 ክፍል ተማሪ ዳሪክ ልሳን ‹‹ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ከ9 እስከ 12 ክፍል እንማራለን። 9ኛ ክፍል እያለን ቀጣይ ክፍሎች ስትደርሱ በደንብ ትማሩታላችሁ እንባል ነበር። ነገር ግን አሁን 12ተኛ ክፍል ስደርስ ያየሁት ነገር ከዓመት ዓመት መጽሐፉ ላይ ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ያለው ይዘቱና ገፅ ብዛቱ እየቀነሰ ነው የመጣው›› ትላለች።
ዳሪክ አሁን ላይ በታሪክ መፅሀፍ ላይ በተማርኩት ስለፓን አፍሪካኒዝም መካከለኛ እሚባል እውቀት እንዳገኘች ታምናለች። ሁኖም አሁን ላይ ተማሪው ትምህርቱን የሚያነበው ለፈተና ብቻ በመሆኑ ከትምህርት ባለፈ የፓን አፍሪካኒዝም ታሪክን እንደራሳችን ታሪክ አድርገን እንድናይ፣ ስለፓን አፍሪካኒዝም በደንብ እምንማርበት ነገር ቢፈጠር ስትል ሀሳቧን አካፍላናለች።
የኢትዮጵያ 12ተኛ ክፍል ታሪክ መፅሀፍ ካሉት 9 ምዕራፎች ውስጥ 4ቱ ኢትዮጵያ ተኮር፣ 3ቱ ምዕራባዊያን ተኮር፣2ቱ ደሞ አፍሪካ ተኮር ናቸው። ስለ አፍሪካ ሲያስተምርም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ በካዛብላንካ እና ሞንሮቪያ ቡድኖች መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ በ1963 በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ይገልፃል።
የደቡብ ሱዳን የተማሪዎች የታሪክ መጽሐፍ ላይ ደግሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የፓን አፍሪካኒዝም ውጤት መሆኑን ይገልፃል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያ ሊቀመንበርም አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደነበሩ በፎቶ አስደግፎ ይናገራል።
በግል ትምህርት ቤት 11ኛ እና 12 ክፍል ታሪክ መምህር የሆነው ጌታሰው ጤናው በበኩሉ ስለፓን አፍሪካኒዝም በሚያስተምረው የታሪክ መጽሐፍ ላይ ቁንፅል ሀሳብ ብቻ መኖሩን ገልጾ፤ ከፓን አፍሪካኒዝም ይልቅ ስለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተሻለ ሁኔታ ሰፋ ብሎ እንደሚገኝ ያነሳል፡፡ ‹‹ለፓን አፍሪካኒዝም ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ሰዎች መካከል የአፄ ሀይለ ሥላሴ ድርሻ ተገልጿል። ነገር ግን የሌሎች አፍሪካዊያን ታሪክ በደንብ ስላልተገለፀ እኔ በግሌ ትምህርት ቤት ባለ ቴሌቪዥን በመጠቀም ተማሪዎቼን ለማስተማር እሞክራለሁ›› ሲል ጥረቱን አስረድቶናል።
የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነው አዝመራው አሂባቸው ስለ ፓን አፍሪካኒዝም የ2ተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ጊዜ የተወሰነ መማመሩን ይገልጻል። ዩኒቨርስቲ ከገባ በኋላም ፍሬሽ ማን ኮርስ ሁኖ በተማረበት የታሪክ ትምህርት ላይም ስለ ፓን አፍሪካኒዝም በደንብ እንዳልተማረ ያስረዳል።
የዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ተሾመ ግርማ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲ ላይ ባለው የኮመን ኮርስ ታሪክ ትምህርት ላይ ስለፓን አፍሪካኒዝም በአድዋ ድል ምክንያት እንደተነሳ፣ ነገር ግን ከዛ አለፍ ብሎ ፓን አፍሪካኒዝም ምንድነው እሚለውን ሀሳብ በደንብ እንዳልተገለጸ ያስረዳሉ፡፡ ተማሪዎችንም ስለፓን አፍሪካኒዝም ቁንፅል ሀሳብ ነው እየተማሩ የሚገኙት የሚሉት መምህር ተሾመ የሚቻል ከሆነ ፓን አፍሪካኒዝም ራሱን የቻለ አንድ ትምህርት ሁኖ ከታች ጀምሮ ቢሰጥ መልካም መሆኑን ምክረ-ኃሳባቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ምን ይደረግ?
የኢትዮጵያን እና የፓን አፍሪካኒዝም እንቅሰቃሴን የትናንት ግንኙነት ስንመለከት ጠንካራ ሁኖ ሳለ ለምን ይህንን ታሪክ ለትውልዱ ማስተማር ደከምን? ለምንስ ችላ ተባለ? የሚለው ጥያቄ መነሳት የሚገባው ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ በአድዋ አማካኝነት የፓን አፍሪካኒዝም ማሳያ፣ የጥቁሮች መገለጫ ሆናለች። የዘንድሮው 129ኛዉ የዓድዋ ድል በዓልም "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል " በሚል መሪ ኃሳብ ነው ተከብሮ የዋለው።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በይፋ «ነፃነት ለማምጣት የሚታገሉ የአፍሪካ ወንድሞቻችን ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊ ሥልጠና መውሰድ ይችላሉ» ሲሉ የገለፁ መሪ ነበሩ። በዚህም አፓርታይድ ሥርዓትን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወገድ የታገሉት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ተገኝተው ወታደሪዊ ሥልጠናውን ወስደዋል፡፡ በአንድ ወቅትም ሲናገሩ "Ethiopia has always held a special place in my own imagination and the prospect of visiting attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African. / ኢትዮጵያ ሁሌም ለእኔ ልዩ ነች። ፈረንሳይን፣ እንግሊዝን እና አሜሪካን በጋራ ከመጎብኘት ይልቅ ልጎበኛት የምጓጓላት ነች። ወደ ኢትዮጵያ መሄድ የአፍሪካዊነቴን ምንጭ የማወቅ ያህል እንደሆነ ይሰማኛል።" ብለው ነበር፡፡
ሌላኛው ጃንሆይ ወደ አፍሪካ መመለስ ለሚሻ ጥቁር ይሁን በማለት ሻሸመኔ አካባቢ 200 ሄክታር ገደማ መሬት መለገሳቸው ይታወቃል። አሁን ላይም ሻሸመኔ ውስጥ በርካታ አፄ ኃይለ ስላሴን እንደ ፈጣሪ ኢትዮጵያንም የቃል-ኪዳኗ ምድር አድርገው እሚያዩ ጃማይካዊያን ይኖራሉ። ታዋቂው ጃማይካዊ ፓን አፍሪካኒስት የሆነው ማርከስ ጋርቬይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ፋና ወጊ እንደሆችና ነፃ አፍሪካን የመፍጠር አርዓያ አድርጎ ይጠቅሳታል፡፡ በአንድ የታወቀ ንግግሩ ላይም “Wake up Ethiopia! Wake up Africa! Let us work towards the one glorious end of a free, redeemed, and mighty nation./ ተነሽ ኢትዮጵያ ! ተነሺ አፍሪካ! ለነጻ፣ ጠንካራ እና ኩሩ ሀገር በጋራ እንስራ።" ሲል ተናግሯል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያን ያለው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የአድዋ የድል በዓልን ወይም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን አስመልክቶ በሚዲያዎች ከሚነገረው የዘለለ አለመሆኑ ለታዘበው ግልጽ ነው፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጥያቄ መንገዱ ጭምር ነው፡፡ ታዲያ ብዙ መጽሐፍት በዚህ ዙሪያ ቢታተሙም፤ ብዙዎች ኢትዮጵያ ስላበረከተቸው አስተዋጽኦ ቢከትቡም እኛ ግን በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖብን ለትውልዱ ማስተማር ያለብንን ሳናስተምር ቀርተናል፡፡
ታሪክ የትውልድ ቅብብሎሽ ነው፡፡ አንዱ መንገዱ ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ በሌላው ዓለም ትውልዱ አንዲማርበት ብቻ ሳይሆን የእኔነት ስሜት እንዲሰማው፤ ታሪኩን እንዲቃኝ እና ጠንካራ አቋም እንዲኖረው በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ አካቶ ማስተማር ትልቁ ስልት ነው፡፡ ብዙ የምናፍርባቸው ታሪኮችን በምንማርበት ትምህርት ሥርዓታችን የጋራ የሚያድረገንን እና በዓለም መድረክ የሚያኮራንን እኛነታችንን በቁንጽል ማስተማር ሊያሳፍር የሚገባ ስብራታችን ነው፡፡ በጊዜም ሊታረም ይገባል፡፡