post-thumb

በ C3 AI ስም የተሰራው ማጭበርበር

ሲ3ኤአይ (C3 AI) በሚል ስም በትርፍ ሰዓት ኦላይን ላይ በመስራት ታተርፋላችሁ ተብለው ሥራ ብለው በገቡበት ብዙዎች በርካታ ብሮችን እንደከሰሩ እና ገንዘባቸውን እንደተጭበረበሩ ከጅማ፣ ከጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ከባሌሮቤ እና ከበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታ አቅርበዋል።

ትሰሩታላችሁ የተባሉት ሥራም በተዘጋጀው ድረ-ገጽ ላይ ይወጣሉ የተባሉ ሰርቨሮችን መከራየት እና የሚገኘውን ኮሚሽን መካፈል እንደነበር ነው የነገሩን። ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ አባላት ሲያስመዘግቡ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንዳሉት ተነግሯቸው ወደ ሥራው እንደገቡ ነው የገለጹት፡፡

የተሰጣቸው ተስፋም 500 ብር ኢንቨስት ቢያደርጉ በቀን 25 ብር ከመስራት ጀምሮ በትላልቅ ብሮች ሰርቨር በሚከራዩነት ወቅትም የትርፍ ኅዳጉ ይጨምራል የሚል ነበር። በዚህ መንገድ የሰሩ ትርፍም ያገኙ ቢኖሩም መልሰው ትርፋቸውን ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ሰጥተው ቀልጠዋል፡፡ በትንሹ የጣማቸው ትርፍ በብዙ አክስሯቸዋል፡፡

ድርጅቱ አገልግሎት ሰጥበታለው ሲል የነበረውን ድረ-ገጽ ዘግቶ የጠፋው ሰኞ ሚያዚያ 13 ቀን ከቀኑ 6 ሰዓት በኋላ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የተናገሩ ሲሆን ከዚያ በፊት ባሉት ቀናት በርካቶች ለበዓል ወጪ ጠይቀው እንደነበር ነግረውናል፡፡

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከ200 ሺ ብር በላይ ተጭበርብረናል ያሉ በርካታ ሰዎችን ያናገረ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የተጭበረበሩ እንዳሉም ሰምቷል። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በተለያዩ ስልቶች በርካቶች ቢጭበረበሩም ብዙዎቹ "ይህ ይለያል፤ ያሳመነን መንገድም ከሌሎቹ ልዩ ነው" ሲሉ ይጠቅሳሉ።

ምን የተለየ ነገር አለው ?

  • ህጋዊ ንግድ ፈቃድ አለው

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተውና ሲስሪ ኤአይ ቴክኖሎጂ / SEE THREE AI TECHNOLOGY PLC የሚለው የንግድ ፈቃድ ጥር 2 ቀን 2017 መውጣቱን የሚጠቁም ሲሆን ሥራዎች ሲሰሩ የነበረው እንዲሁም አባላትን የማሳመን ሥራ ሲሰራ የነበረው በዚሁ ንግድ ፈቃድ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል፡፡ የድርጅቱ የግብር መክፈያ ቁጥር (0093931744) በኢ ትሬድ ማረጋገጫ ህጋዊ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በ3 ሚሊዮን ብር ካፒታል መመዝገቡንና አድራሻውም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 8 የቤት ቁጥር 818 ስር መሆኑን ይገልጻል፡፡

በርካቶች ተጭበርብረንበታል ያሉት ንግድ ፈቃድ

በርካቶች ተጭበርብረንበታል ያሉት ንግድ ፈቃድ

በርካቶች "ይህንን ህጋዊ ንግድ ፈቃድ አይተን ነው የተሸወድነው" ሲሉ ቢገልጹም ንግድ ፈቃዱን ከመመልከት በዘለለ ቅሬታቸውን የገለጹልን በሙሉ በሚባል መልኩ በአካል በድርጅቱ ቢሮ ሄደው እንደማያውቁ፤ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የተባለውና በንግድ ፈቃዱ ላይ ስሙ የሰፈረው ተስፋማርያም ቢሰጥ የተባለውን ግለሰብም በአካል እንዳላገኙት ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተስፋማርያም ቢሰጥን ለማግኘት በተጠቀሱት ስልኮቹ እንዲሁም በቴሌግራም አድራሻው ቢሞክርም ለጊዜው ስልኩ ዝግ በመሆኑ ኃሳቡን ማካተት አልተቻለም።

  • ሚዲያዎች ዘግበውለታል

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለጹት "ድርጅቱ በአሸም፤ በናሁ፣ በባላገሩ ቴሌቭዥን እንዲሁም በሪፖርተር ጋዜጣ በድሬ ቲዩብ የዘገባ ሽፋን ማግኘቱ እንድናምነው አድርጎናል" ሲሉ አንስተዋል። ቲክቫህ ኢትዮጵያ ድርጅቱ ለመቄዶኒያ አረጋዊያን መርጃ ማኅበር ባደረገው ድጋፍ ምክንያት በእነዚህ የሚዲያ ተቋማት የዜና ሽፋን ማግኘቱን ተመልክቷል። ብዙ ሰዎችም ይሄንን ከተመለከቱ በኋላ እምነታቸው መጨመሩንና ገንዘባቸውን ማስገባታቸውን ለመገንዘብ ችሏል።

በመቄኒያ በነበረ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የነበረው የሚዲያ ሽፋን ለሌሎች አባላት መቀስቀሻነት ውለሏል

በመቄኒያ በነበረ የበጎ አድራጎት  ሥራ ላይ የነበረው የሚዲያ ሽፋን ለሌሎች አባላት

መቀስቀሻነት ውለሏል

የዚህ ፕሮግራም አስተባባሪዎች እነማናቸው ?

ይህ ፕሮግራም መጋቢት 28 የተካሄደ ሲሆን በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል 2ተኛ ጠቅላላ ጉባዔ በሚል በቫድማስ ሲኒማ ጠዋት ላይ የተዘጋጀ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የከተማ ጉብኝት እና በመቄዶኒያ አረጋዊያን መርጃ ማኅበር የተዘጋጀ የአረጋዊያንን የእራት የማብላት ሥነ-ሥርዓት ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የክልል አስተባባሪዎች እንዲሁም አባላት ተገኝተው ነበር፡፡

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ጫኔን በስልክ አግኝቶ ቃላቸውን ተቀብሏል። አቶ ጌታቸው ወደዚህ ሥራ የገቡት ከ 5 ወር በፊት እንደነበር ገልጸውልናል። በሰዓቱም እንደማንኛውም ሰው በዋትስ አፕ በተላከላቸው መልዕክት ገብተው የ500 ብር ገዝተው እንደሞከሩ ይናገራሉ።

ከዚያም "ድርጅቱ ትክክለኛ ድርጅት ነው ብዬ በማመኔ ከግሌ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጊያለው፤ ያገኘውትንም ትርፍ መልሼ ኢንቨስት በማድረግ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶብኛል" ሲሉ እንደሌሎቹ ሁሉ መጭበርበራቸውን ያነሳሉ። እሳቸው እንደሚሉት የሚያወሯቸው ሰዎች ሀገር ውስጥ የሌሉ እና በዋትስአፕ ላይ መሆኑን ገልጸው በአካል ከሀገር ውስጥ ያገኙት ሰው እንደሌለ ነው ያስረዱት።

የመቄዶንያው ዝግጅት እንዴት ተካሄደ ?

"ተቋሙ" ቡድን ለሚሰበስቡና ለሚያደራጁ ሰዎች የስብሰባ እና የበጎ አድራጎት ሥራ እንዲሰሩ ገንዘብ እንደሚሰጥ አቶ ጌታቸው ገልጸው በዚህም በእሳቸው ቡድን ያሉ ሰዎችን በማስተባበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመቄዶንያ በመገኘት ለ500 አረጋዊያን ምሳ ማብላታቸውን ይናገራሉ። ይህም በእነሱ በኩል በቅንነት የተደረገ ስለመሆኑ ነው የሚያነሱት።

እነዚህን ሰዎች ለማሰባሰብ እንዲሁም ድጋፍ ለማድረግ ገንዘቡ ከየት መጣ ?

አቶ ጌታቸው÷ ለዚህ ሥራ ከውጪ በእሳቸው አካውንት 500 ሺ ብር እንደገባላቸው በመግለጽ ከዚህ ውስጥ 160 ሺ ብር ወጪ በማድረግ ለአረጋውያኑ ግብዣ እንዳደረጉ፤ ቀሪው ገንዘብ ከቡድናቸው ጋር አዲስ አበባ ላላቸው ስብሰባ የምግብ፤ ትራንስፖርት እና ማደሪያ ወጪ እንደተደረገ ተናግረዋል።

መጋቢት 28 ቀን በተሰናዳው ዝግጅት ላይ

መጋቢት 28 ቀን በተሰናዳው ዝግጅት ላይ

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ይህንን የሚያመላክቱ ፎቶዎች እና ከመቄዶንያ አረጋዊያን መርጃ ማዕከል ለአቶ ጌታቸው ጫኔ ይህንን በማድረጋቸው የተጻፈ የምስጋና ደብዳቤም ተመልክቷል።

እናንተ የተቋሙ አመራር ናችሁ?

በርካቶች እናንተ "የተቋሙ" አመራር መሆናችሁንና አሁንም እናንተን ይጠየቁልን ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ ለዚህ ምን ምላሽ በእናንተ በኩል አለ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ በመለሱት መልስ ‹‹ እኛ ሌሎችን ለማገዝ፤ መረጃ ለመስጠት፤ ለማስተባበር ፊት ለፊት ስለወጣን እንጂ የተለየ ያገኘነው ወይም ሰዎች በእኛ በግል አካውንት ያስገቡት ብር የለም›› ሲሉ የእነሱ ሥራ ማስተባበር እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የመቄዶንያውን ዝግጅት በእሳቸው ቡድን ሥር ያሉ ሰዎችን በማሰባሰብ ያካሄዱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ አይነቱ ስራ የስብሰባ እና የበጎ አድራጎት ሥራ ተብሎ ለቡድን አስተባባሪዎች በሚሰጥ ድጋፍ (ገንዘብ) አማካኝነት የሚደረግ ሲሆን መሰል ስብሰባዎችና የበጎ አድራጎት ሥራዎች በሌሎች ቡድኖች የሚደረጉ ቢሆኑም የእነሱ ሥራ ግን ሚዲያዎች በመኖራቸውና በመቄዶኒያ በመሆኑ ትኩረት መሳቡን ነው የገለጹት፡፡

  • በቅርቡ በስካይ ላይት ሆቴል ትልቅ ዝግጅት ለማድረግ ታቅዶ፤ የአዳራሽ ክፍያም ተከፍሎ ነበር

ሌላው ቅሬታ አቅራቢዎች ያነሱት ሚያዚያ 25 በስካይ ላይት ሆቴል የሚደረግ ዝግጅት ላይ ከVIP 3 በላይ የሆኑ ሰዎችን ለመጋበዝ ታስቦ እንደነበረ እና ለዚህም 1 ሚሊዮን ብር መከፈሉን የሚገልጽ መረጃዎች ልከዋል።

ለስካይላይት ሆቴል ግማሽ መክፈላቸውን የሚያሳይ

ለስካይላይት ሆቴል ግማሽ መክፈላቸውን የሚያሳይ

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው መረጃ ክፍያው የተፈጸመው በአቶ ጌታቸው ጫኔ ሂሳብ ቁጥር እንደሆነ ያሳያል። አቶ ጌታቸውም ይህንን ለማስተባበር እንደተመረጡ እና ለሆቴሉም 500 ሺ ብር ቅድመ ክፍያ መክፈላቸውን የገለጹ ሲሆን ቲክቫህ ኢትዮጵያም ከባንክ ስሊፑ ይህንን መመልከት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ጥያቄውን ለስካይ ላይት ሆቴል አመራሮች ያቀረበ ሲሆን ሆቴሉ የሚሰጠን ምላሽ በፍጥነት ሊደርሰን ባለመቻሉ በዚህ ዜና አልተካተተም፡፡

ሽልማቶች እና ስልኮች ሲሸልሙ ነበር

ሌላው በዚህ ሥራ ብዙዎች እንዲያምኑ እና ገንዘባቸውን እንዲሰጡ ያደረጉት ነገር አጠገባቸው ላለ እና በዚህ ሥራ ላይ እየተሳተፈ ለሚገኝ ሰው የስልክ፣ የሰዓት ሽልማቶችን መስጠታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ሽልማቶቹን ማነው የሚያቀብለው ስንል ስለሁኔታው የጠየቅናቸው አቶ ጌታቸው "ስልኩን ቀጥታ አይልኩም ገንዘብ ይልኩና እነዚህ ልጆች ይሸለሙ ሲባል እዚሁ የሚሰራ ሰው ገዝቶ ለልጆቹ ይሰጣል ልጆቹም ቪዲዮ ሰርተው ይለቃሉ" ሲሉ ይገልጻሉ።

ከዚህ ቀደም ስልክ እንደተሸለሙ የገለጹት አቶ ጌታቸው ሌላ ሰው እንዳቀበላቸው፤ እሳቸውም ለሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ነገር እንዳደረጉ ይናገራሉ።

ገንዘቡ የሚገባው በአንድ አካውንት ስለመሆኑ

ቀደም ብለው የጀመሩ ሰዎች ክፍያ ሲያስገቡ እንዲሁም ክፍያ ሲፈጸምላቸው የተለያዩ የባንክ አካውንቶችን ሲጠቀሙ የቆዩ መሆኑን ቢያስታውሱም ለሦስት እና ለአራት ወር ለሚሆን ጊዜ ግን ቋሚ የባንክ ቁጥር ሲጠቀሙ እንደነበር ይናገራሉ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የባንክ ክፍያዎች ከተፈጸመባቸው ደረሰኞች መመልከት እንደቻለው ክፍያዎቹ ሲፈጸሙበት የነበረው የሂሳብ ቁጥር 1000687201888 R T F IMPORT/Remedan Fako Amana መሆኑን ያመለክታሉ። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበሩ ተመሳሳይ የማጭበርበሪያ መንገዶች ለየት ያለ ይሆናል። በተመሳሳይ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለባንኩ ጥያቄ አቅርቧል ምላሹን እንደደረሰን የምናካትት ይሆናል፡፡

ሌሎች ግን በሦስት ሰዎች የተከፈተ የሂሳብ ቁጥር እንዳለ እና በዚያም የተለያዩ ገቢዎች እንዳሉት ጠቁመዋል። ይሄ አካውንት ዳዊት፣ ጌታቸው እና ዝናሽ በሚል የጋራ አካውንት የተከፈተ ነው። ከሦስቱ አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው "ይህ አካውንት ለመቄዶንያ ከአባላት ድጋፍ ለማሰባሰብ የከፈትነው ሲሉ" ከውጪ የሚመጣ ምንም ገቢ እንዳልነበረው ተናግረዋል። ለዚህም የባንክ ስቴትመንት ማቅረብ እንደሚችሉ ቢገልጹም ባሉት ሰዓት ይህንን ማቅረብ አልቻሉም። አዲስ አበባ በነበራቸው ፕሮግራም ላይ ይህንን የባንክ አካውንት ይፋ ሲያርጉ በዶ/ር ዝናሽ የሚመራ የበጎ አድራጎት ቡድን ማቋቋማቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ከአባላቱ የሚሰበሰበውንም ገንዘብ በሰይፉ ሾው የቀጥታ ሥርጭት ላይ ለማስተዋወቅ እቅድ እንደነበራቸውም በዚሁ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡

የብዙዎች ጥያቄ ምንድን ነው ?

የብዙዎች ጥያቄ ገንዘብ ሲወጣ ሲገባ የነበረበት አካውንት በአስቸኳይ ይታገድልን የሚል ሲሆን የሚመለከተው የህግ አካልም አስፈላጊውን ማጣራት ያድርግልን ሲሉ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በንግድ ፈቃዱ መሰረት ህጋዊ ተቋም የተባለው ድርጅትና ፈቃዱን ያወጣው አካል ይጠየቅልን ሲሉ አንስተዋል።

ንግድ ፈቃዱን በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ እንዳገኘ የምናሳውቅ ይሆናል።

ይሄ ድርጊት የሚፈጸመው ከየት ሀገር ነው ?

ምንም እንኳን C3 AI የተባለው ተቋም በአሜሪካ የሚገኝ ተቋም እና የሚታወቅ ቢሆንም ተመሳሳይ አይነት ሥራ ግን ተቋሙ እንደማይሰራ ከተቋሙ ህጋዊ ገጾች መረዳት ይቻላል። ይሄ ተግባር በዋነኛነት እንደ ዋና ማናጀር የሚታዩት እና በዋትስአፕ ትዕዛዝ የሚሰጡት በአብዛኛው የሀገር መለያ ቁጥራቸው (Country Code) +852 በሆነ ቁጥር ሲሆን ይህም የ ሆንግ ኮንግ (Hong Kong) እንደሆነ ያመለክታል።

በአጠቃላይ በዚህ ሳቢያ በርካቶች ለጭንቀት ተዳርገዋል፡፡ በሌሎች ሲፈጸም ያየነው ዛሬ በሀገራችን ተፈጽሞ እያየነነው ነው፡፡ ስምና ምርታቸው የተለየ ብዙ የማጭበርበሪያ ስልቶች አሁንም ሰዎችን እያጭበረበሩ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከዚህ ትምህርት ሊወስድ ይገባል መልዕክታችን ነው፡፡



Tikvah Ethiopia

Media

ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.