post-thumb

ሱስና አስከፊ መዘዙ!

ሰዎች ለምን የአደገኛ እፆች ሱሰኛ ሰለባ ይሆናሉ?

በኢትዮጵያ ጫት እንዳይቃም መከልከል ይቻላል?

በሱስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው?

በህክምና ከሱስ መላቀቅ ይቻል ይሆን? 

ሱስ የዓይኑን ቆብ ያከበደበት ባለታሪካችን

ቋመኛ ወጣት ቢመስልም ቀስ በቀስ ለጉዳት የዳረገው የሱሱ ዳፋ የዓይኑን ቆብ እንደ ድንጋይ አክብዶበታል። እንደቀልድ የጀመረው ሱስ አንገቱን አስቀርቅሮ፣ ወገቡን አስጎንብሶ እንዲጓዝ ካስደረገው ሰነባብቷል። ባለታሪካችን በአጠቃላይ ቀና ብሎ ለማዬትና ለመጓዝ ሁሉ ይቸገራል።


ለምን ቀና ብለህ አታይም? ተብሎ ሲጠየቅ “እንዴት ነው ቀና ተብሎ የሚታየው?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ያለበት አስከፊ ሁኔታ የሰውኛ አስተሳሰብን ልብ ይሰብራል። ቀጥ ብሎ ማየትና መሄድ ሥነ ምግባር ያልተላበሰ ስለሚያስመስለው ጭምር ቀና ብሎ መሄድን እንደሚፈራ ገልጻል፡፡


እንዲህ አይነት የሕይወት ምስቅልቅል የገጠመው ባለታሪካችን የ28 ዓመት ወጠምሻ ወጣት ነው። ለሞራሉ ደኀንነት ሲባል ስሙ ከመጠቀስ ይቆይ። ወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ፣ አንቱ የሚባል ሙያ ባለቤትም ጭምር ነው! ታዲያ ለ15 ዓመታት በሱስ ተጠቅቷል። ሱስ በርትቶበት በቀን 15 ሲጋራ እንደሚያጨስና ቢያንስ ሦስት ጊዜ ጫት እንደሚቅም ይናገራል። በሌሎች አደንዛዥ እፆችም በሱስ ከተጠመደ ከ10 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ አጫውቶናል።


ታዲያ ይህ ሱስ የዓይኑን ቆብ ያከበደበትና ቀና ብሎ ማየት ሁሉ ያቃተው ወጣት አንድ ጓደኛው እንዴት እንደሚታይ ለወራት ካለማመደው በኋላ ልምምዱ ለውጥ አጎናጽፎት አተኩሮ ሲመለከት በዓይኑ እንባ እያቀረረ ቀና ብሎ ማዬትና መራመድ እንደሞከረ ይናገራል። ይሁን እንጂ ከመቃምም ሆነ ማጨስ ሊታቀብ ቢሞክርም አልተሳካለትም። ሱስ ለማቆም በአቋሙ ባለመጽናቱም ተመልሶ ወደ ነበረበት  አዘቅት መግባቱ እንዳልቀረ አልደበቀም።


ከላይ ከተጠቀሱት አስከፊ የሕይወት ገጠመኞቹ በተጨማሪ ባለታሪካችን በተደጋጋሚ ከሞት ደጃፍ ደርሶ ተመልሷል። ፀበል ገብቷል። ህክምና ሂዷል። ብቻ ብዙ ነገር አድርጓል። ነገር ግን ብርቱ ጽናት ማካበት ስላለበት አሁንም ካለበት አስከፊ ህይወት ለመውጣት ገና ጥረት ላይ ነው። 


“በቀላሉ የጀመርኩት መቃም፣ ማጨስ ሱስ ሆኖኝ ለማቋረጥ ብሞክርም ገና እየዳከርኩ ነው’” ሲል እውነታውን ገልጿል። ይህ ለመንደርሪያ ያክል ያቀረብንላችሁ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ጹሑፋችን በሱስ ቀኝ ግዛት የወደቁ በርካታ ወገኖች የሚገፉትን ምስቅልቅል ህይወትና የሱስን አስከፊ መዘዝ ከባለሙያዎች አስተያዬት ጋር በማጣቀስ በሰፊው የምንመለከት ይሆናል።

ሱስና አስከፊ መዘዙ!

ምሁራን፣ በሱስ ረገድ የተጠኑ ጥናቶች እንዲሁም የጉዳቱ ሰለባዎች ሱስ ዘርፈ ብዙ አስከፊ መዘዞች እንዳሉት መለፈፍ ከጀመሩ ሰንበትበት ቢሉም የሱስ አስከፊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም፡፡ ብዙ የሰማን ስለመሰለን ሱስ ታዲያ በክፋቱ ልክ ተገልጾ ይሆን? በተለያዩ ጊዜያት የሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦችስ ውጤታማ ሆነው ይሆን? ምን ያህል ወጣቶችስ በሱስ ከሚመጣባቸው አስከፊ ጉዳት ቀኝ ግዛት ወጥተዋል? መንግስትስ የሰጠው ትኩረት በምን የሚለካ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሳ ገና ብዙ መነጋገር፤ ብዙ መስራት ያለብን ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማናል፡፡


መቃምም ሆነ ማጨስ ለጤና ጠንቅ፣ በጥቅሉ ሱስ ህመም መሆኑን የሚያውቁት እንኳ በጣት የሚቆጠሩ ዜጎች ባሉባት ኢትዮጵያ የሰው ሕይወት በሱስ እንዳይባክን በቂ ስራ ተሰርቷል ብሎ ደፍሮ መናገር ከፌዝ አይተናነስም ቢባል ማካበድ አይሆንም። ምክንያቱም ባለንበት ወቅት በተለይ በጦርነትና ሥራ አጥነት ችግር የሚናጡ በርካቶች ካሉበት ጭንቀት እንደ መውጫ መንገድ የሚጠቀሙት መቃም፣ ማጨስን መሆኑ የማይሸሸግ መሬት ላይ ያለ ሐቅ ነውና። 


ምሁራንም ጭምር እንደሚሉት ለዛም ነው በርካቶች ሙሉ ጤናቸውን በሱስ ተነጥቀውና ከሰነቁት ብርቱ ዓላማቸው እየተሰነካከሉ በየእሞነት ተቋማቱና በየጎዳናው የሚወድቁት። የሆነው ሆነና ያልተመለሰው ጥያቄ ታዲያ፣ በየአቅጣጫው በጦርነት በምትታመስና የሥራ አጦች ቁጥር በየወቅቱ በሚጨምርባት ኢትዮጵያ የሥራ እድል ማመቻቸቱ ይቅርና ወጣቶች በብስጭት ስሜት የሚዘፈቁበት የሱስ አከፊነት ላይ ከእንጭጩ አመርቂ ሥራ ተሰርቷል? የሚለው ነው። 


የብዙዎች ታሪክ እንደሚያስረዳው በሱስ የመዘፈቃቸው ምክንያት የግንዛቤ እጥረት ነው። በመግቢያችን ታሪኩን ያካፈለን ባለታሪካችንን እንደ ማሳያ ተጠቀሰ እንጂ በዘርፉ አመርቂ ሥራዎች ባለመሰራታቸው በርካታ ወገኖች ግንዛቤው ሳይኖራቸው በተለያዩ አደንዛዥ እፆች ሱሰኛ ከመሆናቸውም ባሸገር የጤና እክል ሲገጥማቸው ይስተዋላሉ።


በዚሁ ረገድ ታሪኩን ያጋራን አንድ ወጣት፣ “ጫት መቃምን ለመዝናናት ብዬ ነበር የጀመርኩት። ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ካልቃምኩ የማልሰራ ሆኜ ራሴን አገኘሁት” ሲል ተናግሯል። “አሁን መቃም ለማቆም ብፈልግም መተው አልቻልኩም። እንደቀልድ የጀመርኩት ድርጊት ይኼው የህይወት ዋጋ እያስከፈለኝ ነው። አብዛኛዎቹ የሚቅሙ ጓደኞቼ በዚህ መልኩ ነው ጀምረው ሱሰኛ የሆኑት” ይላል።

በመግቢያችን የጠቀስነው ባለታሪካችንም፣ “በሱስ ምክንያት ስራዬን በአግባቡ ባለመስራቴ ከአምስት ጊዜ በላይ ከተለያዬ ተቋማት የስንብት ደብዳቤ ተጽፎብኛል። በህመም ምክንያት በ3 ዓመታት ከ15 ጊዜ በላይ ሥራ አቋርጫለሁ” ብሏል። “ሥራዬን ለመስራት በቀን ቢያንስ 15 ሲጋራ ማጨስ፣ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጫት መቃም አለብኝ። ይህን ካላደረኩ መስራት የማልችል መሆኔን የተረዳሁት ግን ሱሰኛ ከሆንኩ በኋላ ነው” ሲልም የገጠመውን ምስቅልቅል አስረድቷል።


ሌላኛዋ ሲጋራ የምታጨስ፣ አልኮል የምታበዛ ባለታሪካችን ደግሞ፣ “ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ከድብርት ለውጣት በሚል እንደቀልድ ነበር ማጨስ የጀመርኩት። በኋላ ግን ከዚህ ህይወት መውጣት ብፈልግም ይሄው ለ8 ዓመታት በዛው ውስጥ እየዳከርኩ እገኛለሁ” ብላለች። ሱስ ያስከተለባትን የጤና ጉዳት በገለጸችበት አውድ ደግሞ፣ “ሳምባዬና ጉበቴ እንደተጎዳ፣ ህክምና ካልተከታተልኩ ጭራሽ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆን ተነግሮኛል” ስትል ተናግራለች።


ታዲያ የሚያሳዝነውና ጥያቄ የሚያስነሳውም ነጥብ ሰዎች በጤንነታቸው እክል እስኪገጥመው ድረስ ዋጋ የሚከፈሉት ለቀልድና መዝናኛ በሚል በሚጀምሩት አደንዛዥ እፆችን የመጠቀም ሂደት መሆኑን እንዲያውቁ ለማስቻል እየተሰጠ ያለው የቅድመ መከላከል ሥራ እንኳ አናሳ መሆኑ ነው።

ሰዎች ሱሰኛ የሚሆኑት እንደቀልድ በጀመሩት የመቃምና ማጨስ ልምድ እንደሆነ፣ መጎዳታቸውን ሲያውቁ ሱሱን ለማቆም ቢፈልጉም እንደሚቸገሩ፣ የተቆራኛቸው ሱስ በጤናቸው ጭምር እንደጎዳቸው የሚያውቁትም ሱሰኛ ከሆኑ በኋላ መሆኑን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራንም ያሰምሩበታል።


በአማኑኤል የአእምሮ ህሙማን ሆስፒታል የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ ማሞ እንደገለጹት፣ ሰዎች በሱስ ተጎጂ እንደሆኑ የሚገባቸው በጣም ዘግይቶ ነው። ባለሙያው በዚሁ ረገድ ባደረጉት ንግግር፣ “ጫት መቃምም ሆነ ሲጋራ ማጨስ ተጠቃሚዎቹን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይከታሉ። ተጠቃሚዎቹ ግን እንደተጎዱ የሚያውቁት ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው” ሲሉ የመዘዙን ድብቅነት አስረድተዋል።


ሱስ በጤና ጭምር የከፋ ጉዳት እንደሚያስከትል ሲገልጹ ደግሞ፣ “የሱስ ጉዳቱ በአንዴ ስለማይታይ፣ አንዳንዱ ጉዳት ደግሞ ውስጣዊ ስለሆነ በየትኛውም ደረጃ ያለ ተጠቃሚ በሱስ ውስጥ ካለ ማወቅ ያለበት ቀስ እያለ የሚገልድል ህመም ውስጥ መሆኑን ነው” ብለዋል።


“በዓለም ላይ ገዳይ ከሚባሉት ህመሞች አንዱ ሱስ ነው” ያሉት አቶ እንዳለ፣ “አንድ ሰው ለረጅም ጊዜ ሱስ ውስጥ ይቆያል ስንል ፈልጎት ራሱን የመግደል ሙከራ ውስጥ ነው እንደማለት ነው!” ሲሉም በአንክሮ አስገንዝበዋል።


አክለውም፣ “ግን ከረጅም ጊዜ መጠቀም በኋላ ነው ሰዎች ራሳቸውን በሱስ ተጎድቶ የሚያገኙት” ሲሉ ባለታሪኮቻችንን ያካፈሉንን በሱስ መጠቃታቸውን ዘግይቶ የማወቅ ገጠመኝ በመጋራት ሀሳባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በእፆች ሱሰኛ የሆኑ ወገኖች ከሚያደርስባቸው የጤና እክል በተጨማሪ የለመዷቸውን እፆች ካልተጠቀሙ ሥራ መስራት እንዳይችሉ መገደዳቸው ደግሞ ሌላኛው የሱስ አስከፊ መዘዝ መሆኑ ተመላክቷል።


በዚሁ ረገድ ደግሞ የሱስ ማገገሚያ ተቋማት እንደሚሉት፣ አብዛኛዎቹ ጫት የሚቅሙ፣ ሲጋራ የሚያጨሱና ሌሎች አደንዛዥ እፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ካልቃሙና ካላጨሱ ለመስራት እንደሚቸገሩ በጥናት ተረጋግጧል።


በኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች፣ ከዚህ ቀደም በቀጥታ የጫት ሱስ ካለባቸው 1,300 ሰዎች ላይ ጥናት ሰርተው እንደነበር የገለጹት የ “እሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን” ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ፣ አብዛኛዎቹ ጫት ቃሚዎች ካልቃሙ ሥራቸውን መስራት እንደማይችሉ በጥናት መታወቁን ተናግረዋል።


በገለጻቸው መሠረት፣ በጥናቱ ከተለዩት ምላሽ ሰጪዎች ውስጥ 33 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ሱሰኞች መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ በዚህም “ጫት ካልቃሙ መስራትና መንቀሳቀስ አይችሉም” ሲሉ አውስተውላቸዋል።


የአደንዛዥ እፆች ሰለባ የሆኑ ወገኖች የሱስ ልማዳቸውን ካላደረሱ ሥራቸውን ለመስራት እስከመቸገር ከመድረሳቸው ባሻገር፣ ለቀልድና መዝናኛ በሚል የሚጀምሩት እፆቹን የመጠቀም ሂደት ሲከፋ ደግሞ ቀስ በቀስ ለከፋ የጤና መታወክ እንደሚያጋልጣቸው የባለታሪኮቻችንን ሀሳብ በመጋራት አቶ ሲሳይ አስምረውበታል። 


በዚህም የሚቅምን፣ የሚያጨስን ሰው እንደ ዘመናዊ አድርጎ መቁጠር፣ ሳያስቡት ለጨዋታና ለቀልድ መሞከር፣ ከድብርት መውጫ አድርጎ በማሰብ አደንዛዥ እሰፆችን መጠቀም መጀመር ሱሰኛ ሆኖ በመቅረት ለጤና እክል የሚዳርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።


“ሱስ የተያዙ ሰዎች ሱስ ውስጥ መሆናቸው አይታያቸውም። ግን ሁልጊዜ ሱስ ውስጥ ነው ያሉት። ከዚያ ለመውጣትም አይችሉም” የሚል ኃሳብ ያነሱ ሲሆን፣ የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ ማሞም ብዙ ሰዎች አደንዛዥ እፅን ካሉበት መጥፎ አጋጣሚ ለመውጣት ይረዳናል በሚል እሳቤ ወደ ሱሰኝነት እንደሚገቡ ይስማማሉ።


“ሱስን በደንብ መረዳት ይኖርብናል። ሱስ ስንል ከሰውነታችን ጋር በደንብ ተዋህዶ ያለ ጥገኛ ነገር ነው። መዋሃዱ ከሰውነት አካል ክፍሎች ጋር ይገናኛል። ሰዎች ‘ካለሱማ’ የሚሉበት አስተሳሰባዊ ተዛምዶም አለው” የሚሉት ባለሙያው፣ ሰዎች ለጭንቀት፣ ለድብርትና ለሥራ ማስኬጃ በሚል አደንዛዥ እጽን እንደ አጋዥ አድርገው እንደሚያስቡ ገልጸው፣ “ስለዚህ ሱስ አስተሳሰባዊም ጭምር ነው” ብለዋል።


የህክምና ባለሙያው፣ “አንዳንዱ ሰው ደግሞ ሱስን አጠቃላይ ችግር መፍቻ አድርጎት ይስተዋላል። ሲጨነቁ፣ ከቤተሰብ ጋር ሲጣሉ፣ ሲደብራቸው ከዛ መውጫ ስሜት አድርገው ይወስዱታል” ሲሉም ሰዎች የተሳሳተ አስተሳሰብን በመተግበር በሱስ አሮንቃ እንደሚዘፈቁ አስረድተዋል።

“አደንዛዥ እፆችን መጠቀምን እንደ ትክክለኛ መንገድ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ” ያሉት ባለሙያው፣ በቶሎ ስለማይከሰት እንጂ አስከፊ ጉዳት እንዳለውና ትክክለኛ ምርጫ አለመሆኑን ሲያስረዱ ደግሞ፣ “ጉዳቱ በቶሎ ስለማይታይ ነው። ከረጅም ጊዜ መጠቀም በኋላ ነው የሱስ ጉዳቱ የሚታየው።  ያኔ ነው ሰዎች ደግሞ መጎዳታቸውን የሚያውቁት” ሲሉ ተናግረዋል።


ለመሆኑ ሰዎች በጤናቸው እክል የሚያስከትል የሱስ ሕይወት ውስጥ የሚገቡት ለምን ይሆን? የማይፈልጉትና የማይወጡት የሕይወት አዘቅት መግባትን ፈልገው? ወይስ መቃም ማጨስ እፎይ መባያ ሲመስላቸው የአደንዛዥ እፆች አቅርቦት በየቦታው በማገኘታቸው? ነው ወይስ ምቹ መዝናኛ ስለማያገኙ? ሰዎች ለምን የአደንዛዥ እፆች ሱሰኛ ይሆናሉ? እነዚህ የብዙዎች ጥያቄዎች ናቸው።

ሰዎች ለምን የአደገኛ እፆች ሱሰኛ ሰለባ ይሆናሉ?

ሰዎች ለምን ወደ ሱስ ህይወት መግባትን ይመርጣሉ? የሚመለከታቸው አካላትስ ችግሩ እንዳይስፋፋ ምን ያክል ትኩረት እየሰጡ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች የበርካቶች ናቸው።


በቀጣዩ ክፍል ታሪካቸውን በሰፊው ያጫወቱን ለ22 ዓመታት በሀሽሽ፣ ሲጋራና ሌሎች አደንዛዥ እፆች ሱስ ሲዳክሩ እንደኖሩ የሚናገሩት አቶ ዮናታን ሊዮን የተባሉ ባለታሪካችን፥ ሥራ አጥነት፣ ብስጭት፣ ጦርነት፣ ድብርት ሰዎችን የአደንዛዥ እፆች ተጠቃሚ እንደሚያደርጓቸው ከገጠመኛቸው በመነሳት ያስረዳሉ።


ቀጥለው የመፍትሄ ሀሳቡን ሲያጋሩ ደግሞ፣ ሰዎች ሥራ አጥ ሲሆኑ፣ የድብርት ስሜት ሲሰማቸውም ሆነ ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው፣ አደንዛዥ እፆችን ለመጠቀም መፍቀዳቸው ከገጠማቸው ችግር መውጫ በር እየዘየዱ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ሌላ አስከፊ መከራ እየጠሩ መሆናቸውን ሊያውቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አንድ የሰሜን ወሎ አካባቢ ወጣት ባጋራን ሀሳብ፣ በተለይ ወጣቱ ክፍል ቃሚና አጫሽ የሆነው ጦርነትና ሥራ አጥነት በሚስተዋልበት ወቅት መሆኑን ከምልከታው በመነሳት ይናገራል። “በኛ አካባቢ ጫት መቃም የቆዬ ቢሆንም ሰው ሙሉ ጊዜ ሰጥቶ ቁጭ ብሎ አይቀምም ነበር። ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ግን በተለይ ወጣቱ ክፍል ውሎና አዳሩ ጫት መቃም ሆኗል። ምክንያቱም መሄጃ የለውም” ነው ያለው።


በተለይ ጦርነትና ሥራ አጥነት ሲስፋፋ አምራች የሚባሉት ወጣቶች ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ አገራቸውን ከዚህ አልፎ ዓለምን መጥቀም በሚችሉበት ወቅት ሳያስቡት ሱሰኛ እንደሚሆኑ ምሁራኑም ጭምር ያምኑበታል።


ጦርነትና ሥራ አጥነት ሱሰኝነትን እንደሚያስፋፉት የሚጋራው እሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የሱስ ማገገሚያ ተቋም፣ ጫት መቃም ወደ ምሥራቁ (ወደ ድሬዳዋና ሀረር) የተለመደ ሆኖ ቢቆይም በሰሜኑ (ወሎና መቐለ) ግን እምብዛም ያልተመደ እንደነበር አስታውሷል። ሆኖም ግን በተለይ ከጦርነት በኋላ በሰሜኑ በኩልም ጫት የመቃም አዝማሚያ መስፋፋቱን ድርጅቱ ገልጿል።


ከዚህ ቀደም በድርጅታቸው የተጠናቀረውን ጥናት መሠረት በማድረግ በየትኛው የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ናቸው በብዛት ወደ ሱስ የሚገቡት? ምክንያታቸውስ ምንድን ነው? ስንል የጠየቅናቸው አቶ ሲሳይ ታረቀኝ፣ ጥናቱ እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 በሆኑ ወጣቶች እንደተሰራና አብዛኞቹ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የአደንዛዥ እፆች ሱሰኛ መሆናቸው እንደታወቀ አስረድተዋል።


ለምንድን ነው ወደ ሱስ የምትገቡት? በሚል በወቅቱም እንደጠየቋቸው አስታውሰው፣ እንደ ወጣቶቹ ምላሽ ደግሞ፣ "ብዙዎቹ የኢኮኖሚ ጉዳይ፣ የማዘውተሪያ ቦታ እጥረቶች ያነሳሉ። በስራ አጥነት ተስፋ ከመቁረጥ ጋርም ይገናኛል" ብለዋል።


የወጣቶች ማዕከላት፣ ክለባቶች፣ ቲያትር፣ የፀረ ኤድስ፣ የስነ ተዋልዶ ጤና ክበባት ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በስፋት ስለነበሩ ወጣቶቹ በዚያ በመዝናናት ወደ ሱስ የመግባት እድላቸው ጠባብ እንደነበር ገልጸው፣ "አሁን እነዛ የወጣት አደረጃጀቶች ብዙ አለመኖራቸው፣ የማኀበራዊ ሚዲያውም ተፅዕኖ ወጣቶች ወደ ሱስ እንዲገቡ የሚገፋፉ ምክንያቶች ናቸው" ሲሉ ክፍተቱን አመላክተዋል።


ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ ታዲያ ወቅቱን የጠበቀ መፍትሄ እየተሰጠ ነው ወይ? በግንዛቤ እጥረት ጭምር ሰዎች የሚዘፈቁት ከአደዛዥ እፆች መካከል ተጠቃሽ በሆነው በጫት ሱስ የሚዳክሩ ሰዎችንስ እንዴት መታደግ ይቻላል?

በኢትዮጵያ ጫት እንዳይቃም መከልከል ይቻላል?

የጫትን ጉዳይ ብቻ ብንመለከት እንኳ፣ ዘርፈ ብዙ ጥቅሙንና ጉዳቱን በማንሳት ብዙዎች የተለያዩ የሙግት ሀሳቦችን ያንሸራሽራሉ። አንዳንዶች፣ “በኢትዮጵያ ጫት መቆም የለበትም። አንዱ የገቢ ምንጭም ነው። ሰው ነው መቃሙን ማቆም ያለበት” ሲሉ ይደመጣሉ። ሌሎች ደግሞ፣ “ጫት ኢትዮጵያ ውስጥ ክልከላና የተለዬ ህግ ያስፈልገዋል” ይላሉ። በሌላ ወገን ያሉት ደግሞ፣ “ጫት ክልከላ ሳይሆን ቁጥጥር ነው የሚያስፈልገው” በማለት ይሞግታሉ። 


ጫት የኢዮጵያ ውስጥ ክልከላና የሕግ ድንጋጌ ያስፈልገዋል ሲሉ የሚያስገነዝቡ ድርጅቶች አሉ። ይህን የሚሉት ብዙዎች ጫት ቃሚ የሆኑት ክልከላ ስላልተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ነው። ለአብነት፣ የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ በዚሁ ጉዳይ ተመስርተው ሲናገሩ፣ ለብዙዎች ሱሰኛ መሆን ምክንያቱ እንደሌሎች የአልኮል መጠጦችና አደንዛዥ እፆች ጫት ላይም ክልከላ ባለመደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ።

ጫት አደንዛዥ እፅ መሆኑንም ብዙዎች እንደሚዘነጉት አስረድተው፣ ‘እንዳይቃም’ ተብሎ ባለመከልከሉ ማንም በትራንስፖርትና በፈለገበት ቦታ እንደሚጠቀመው ጠቅሰው፣ “ክልከላ ያስፈልገዋል። ጫት አንዱ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገር ነው” ብለዋል።

የተለየ ህግና ክልከላ ባለመኖሩ ጫት ያስከተለውን መዘዝ በገለጹበት አውድ ደግሞ፣ “ብዙ ወጣቶች በጫት ሱሰኞች ሆነዋል። ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን በጫት ያጠፋሉ። ማህበራዊ ህይወታቸው ተበላሽቷል” ያሉ ሲሆን፣ ማህበረሰቡም ግንዛቤ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፣ “ጫት ክልከላ ይደረግበት” ሲሉ ተናግረዋል።

እውነት ጫትን መከልከል ይቻላል ወይ? በዚህ ረገድ የሌሎች አገራት ተሞክሮስ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


“አሁን ባለው ሁኔታ ጫትን ሙሉ ለሙሉ ከሀገራችን እናስቁም ብንል አንችልም። ምክንያቱም ከአምራቹ እስከ ቃሚው ብዙ ሰንሰለት አለው። በጫት ኑሯቸውን የመሰረቱ፤ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ብዙ አካላት አሉ። ግን ልክ እንደ ሲጋራው፣ እንደ መጠጡ ጫትም ገደብ ያስፈልገዋል” በሚል ሙግታቸውን ያብራራሉ። “በተለይ ወጣቶች እንዳይቅሙ በእድሜ፣ በቦታ መገደብ አለበት። የክልከላ ህጎች ቢኖሩ ተጠቃሚውን ይቀንሰዋል። ትልቁ መሰራት ያለበት የህግ ክፍተቱ ላይ ነው” ብለዋል።

ከጫት ክልከላ ጋር በተያያዘ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያም፣ “ጫት በምዕራቡ ዓለም ብዙ አይታወቅም፤ ከጫት ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ ያሉት ሀገራት እኛ አካባቢ ያሉ ካልሆኑ በስተቀር። ከዚህ አንፃር ተሞክሮ ማገኘት አልተቻለም። ይሄ ጉዳይ በይበልጥ የኛ ሀገር ጉዳይ ስለሆነ” ሲሉ ከአገራት ተሞክሮ እንዳልተገኘ አስረድተዋል።


ሆኖም ግን የጫት ክልከላ ሕጉ እንደሚያስፈፍግ በአንክሮ ገልጸው፣ “የጫት ክልከላ አዋጅ ተጀምሮ ነበር። በፓርላማም እንዲጸድቅ ሙከራዎች ተደርገው ነበር። ህጉ በተመሳሳይ ከአልኮል ከመጠጥ ጋር እኩል የተጀመረ ነው። በመጣጥ የተደረገውን የገደብ ሂደት ተከትሎ እንዲሄድ ተጀምሮ ነበር። ከዚያ በኋላ የት እንደገባ ሳይታወቅ ቆይቷል የጫት ጉዳይ” በማለት ተናግረዋል።


“የአልኮል እና የሲጋራ ህግ በአዋጅ ወጥቶ ሰው ማጨስ የሚችለው ማጨስ የሚፈቀድባቸው ቦታዎች ነው እንጂ ትራንስፖርት፣ መጠጥ ቤት ላይ ማጨስ ክልክል ነው። ማስታወቂያ አይነገርም ቁሟል” ብለው የጫት ህግም በአዋጅ ሊጸና እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፖለቲካና ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ጭምር በጫት ሱስ እንደተዘፈቁ አስረድተው፣ “የጥቅምም ጉዳይ ስላለው እንዲገፋም ያልተፈለገበት ምክንያት ሊኖር ይችላል። ግን ውትወታ፤ ብዙ አካላትን የቅንጅት ስራ ይፈልጋል” ሲሉም ሕጉን ማጠንከር እንደሚገባ አስተያዬት ሰጥተዋል።

በመጨረሻም፤ ለጊዜው ቁጥጥር እንዲደረግበት፣ ለመጨረሻው ግን ጫት ክልከላ እንዲደረግበት ለምሳሌ በዕድሜ፣ በቦታ እንዲገደብ፣ የመቆጣጠሪያና የመከላከያ ቁጥጥር ህግ እንዲኖር የውትወታ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በሱስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው?

ለመሆኑ በተለይ የጫት ተጠቃሚዎች ቀጥር እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ? መፍትሄውስ ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች የሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ማብራሪያ በስንት እንደጨመረ ተጨማሪ ለማወቅ ጥናት ቢያስፈልግም እየጨመረ መሆኑን አልደበቀም።


በተቋሙ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዱለጢፍ መሀመድ፣ “በትምህርት ቤቶች፣ በክልሎች የተለያዩ ድጋፎችን ስናደርግ የሱስ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ” ሲሉ ቁጥሩ እየጨመረ መሆኑን አስረድተው፣ ሁሉንም ተቋማት ያካተተ አንድ ጥናት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።


ችግሩን ለመቅረፍ ከቤተሰብ ጀምሮ ጠንካራ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው  ያሳሰቡት ኃላፊው፣ “በአንድ ተቋም ብቻ ወጣቶች ላይ ተሰርቶ ምንም ውጤታማ አይኮንም” ሲሉ ዘርፉ የቅንጅት ስራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል። “እንደ ተቋምም እንደ ማኀበረሰብም ስንሰራ ደግሞ ከሱስ ነጻ የሆነ ተቋምን፣ ሱስ የሚጠየፍ ማህበረሰብ መገንባት ያስፈልጋል” ሲሉም የመፍትሄ ሀሳብ አጋርተዋል።

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሻገር ሌሎች ተቋማት የሱሰኞች ቀጥር እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ። የሱሰኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ማለት ይቻላል? የሚል ጥያቄ ያቀረብንለት በሱስ ሳቢያ የተጎዱ ሰዎች ህክምና የሚከታተሉበት አማኑኤል የአእምሮ ህሙማን ሆስፒታል፣ በስንት ጨመረ ለሚለው ጥናት ቢያስፈልገውም፣ የሱሰኞች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጿል።

በሆስፒታሉ የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ ማሞ፣ “ኤግዛክት ቁጥሩ ይሄ ነው ማለት አንችልም። የቅርብ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በተለይ የወጣቱ ክፍል ተጠቂ የመሆን ቁጥራቸውን እየጨመሩ ካሉ ህመሞች አንጻር ሱስ አንደኛውን ድርሻ ይወስዳል” ብለዋል።


በሆስፒታሉ ያሉት አብዛኛዎቹ የአዕምሮ ህመም ታካሚዎች ከሱስ ጋር ከፍተኛ ተዛምዶ ያላቸው መሆናቸውን የተናገሩት የሥነ አዕምሮ ህክምና ባለሙያው። “ቁጥሩም እያየለ ነው። ተኝተው ከሱስ ለማገገም የሚመጡ ታካሚዎች ብቻም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

የሆስፒታሉ የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፓርት በሚያስረዳው መሠረት ደግሞ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ብቻ ለ66 ሺሕ 741 ሰዎች የሥነ አእምሮ ህክምና የተሰጠ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም 410 የሚሆኑት ከሱስ ጋር በተገናኘ ህክምና ያገኙ መሆናቸውን ሪፓርቱ ያሳያል።


የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ በበኩላቸው፣ “ከሌላ ጊዜ አንጻር ለሱስ ህክምና ብቻ የሚመጡ ታካሚዎች አሉን በተመላላሽም ተኝቶ በሚታከሙ” ብለው፣ “ከሌላው ጊዜ አንጻር ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል” ሲሉ ግልጸዋል። 


በመሆኑም በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ አቅርቦቱ በመስፋፋቱ በተለይ ጫት ላይ ልዩ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን እያስገነዘቡ ሲሆን፣ ለመሆኑ የጫት ሱሰኞችን ለመቆጣጠር በትኞቹ ቦታዎች ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይገባል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን” ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ፣ “አሁን የትም ማለት አይቻልም” ብለው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደተስፋፋ ተናግረዋል።

“ችግሩ እንደ ሀገር ነው። ይሄ ቦታ ብቻ ነጻ ነው የሚባል ቦታ የለም። በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ችግሩ ስፋፍቷል። የትም አካባቢ ጫት የማይሸጥበት ቦታ አይገኝም ኢትዮጵያ ውስጥ” ሲሉ ገልጸዋል።

ምን በጀ?

በአደንዛዥ እፆች ሱስ ተዘፍቀው ዘርፈ ብዙ ችግር እያስተናገዱ ያሉ ወገኖች ካሉበት ህይወት እንዲወጡ፣ ሌሎቹም አስከፊነቱን ተገንዝበው ወደ ሱስ ከመግባት እንዲቆጠቡ እንደ ሀገር ምን መደረግ እንዳለበት ምሁራን ሙያዊ ምክር ለግሰዋል።


የሥነ ልቦና ባለሙያው ቴዎድረስ ድልነሳው በሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ፣ “ሱስ እንደ ህመም ነው የሚታየው በትልቁ ሥነ አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ክፍል” ይላሉ።


“ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ሰዎች የየትኛውም ነገር ሱስ ምርኮኛ ከመሆን መታቀብ እንጂ ሱስ አንዴ ሰዎችን ከተዋሃደ መውጫው ሩቅ መሆኑን ባስረዱበት አውድ፣ “ብዙ ጊዜ ማገገሚያ ገብተው ተመልሰው ሲወጡ ሰዎች ሱሱን ይቀጥሉበታል” ሲሉ ያስተዋሉትን ተናግረዋል።


ሱሰኛ ለጊዜው እንጂ ሙሉ በመሉ ሱስን አያቆምም ተብሎ እስኪቀለድ ድረስ ሰዎች ማገገሚያ ከገቡ በኋላ ወደ ሱስ እንደሚመለሱ ገልጸው፣ ተመልሰው በሱስ የሚዘፈቁትበት ምክንያት ደግሞ በማገገሚያ ተቋማት የሱሰኞቹ ጥልቅ ችግራቸው ከመሰረቱ ተደራሽ ስለማይደረግ መሆኑን አስረድተዋል። በዚሁ መልዕክታቸውም የየተኛውም አደንዛዥ አፅ ሱሰኛ ባለማድረግ ራስን መርዳት ግንባር ቀደም መፍትሄ መሆኑን ልብ ይሏል።


“የሱስ ህክምና በጣም አክሳሪ ነው።  ማገገሚያ የገቡ ሰዎች እስከ 90 በመቶ ድረስ ወደ ሱስ ሊመለሱ ይችላሉ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሟልቶ እንኳ” ሲሉም ከምንም በላይ ወደ ሱስ አለመግባት የማያሻማ ተመራጭ መንገድ መሆኑን መክረዋል። 

ይህ ሙያዊ ምክር ገና ወደ ሱስ ያልገቡ ሰዎች ሊረዱት የሚገባ የማስጠንቀቂያ ደውል ሲሆን፣ የሱስ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለይ ህክምናቸውን በቆራጥነት መከታተል ከችግሩ መውጫ መንገዳቸው መሆኑ ተጠቁሟል።


በሌላ በኩል የሱስ ተጠቂዎች ቁጥር በየወቅቱ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ በቂና የተሟሉ የሱስ ማገገሚያ ተቋማት አለመኖር ሌላኛው የችግሩ መንስኤ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ምሁራን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።


የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴበሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የሱስ ማገገሚያ ተቋም እንደሚለው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ያሉ የማገገሚያ ተቋማት በዛ ቢባል ከአምስት የማይበልጡ ሲሆን፣ አብዘኛዎቹ ደግሞ የበጀት ችግር ይፈትናቸዋል። 


በቂ የሱስ ማገገሚያ ተቋማት አሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ያቀረብንለት ድርጅቱ፣ “በተለይ ጫት ላይ የሚሰራ ተቋም ብዙ የለም። ለምሳሌ በስነ ተዋልዶ፣ ጤና፣ በኤች አይ ቪ ላይ በጣም ብዙ ድርጅት ማግኘት ይቻላል። ከሱስ ጋ ተያይዞ ግን በጣም ውስን ድርጅቶች ናቸው የሚሰሩት” ሲል ክፍቱን አጋልጧል። “በቂ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትም የሉም። በቁጥር ናቸው። የሱስ ማገገሚያ ብዙ ማዕከላት የሉምና እሱም አንዱ ችግር ነው” ብሎ፣ ለዚህም ልዩ ተኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል። 

“ወጣቶች ተስፋ ሲቆርጡ፣ ስራ ሲያጡ ያላቸው አማራጭ ጊዜያቸውን የሚያጠፉበት መንገድ ሱስ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተደራርበው የወጣቶችን በሱስ ተጋላጭነት በጣም አስከፊ አድርጎታል” ሲልም አስረድተዋል።

በኮቪድ ወቅት ወጣቱ በሱስ ተዘፍቆ እንደነበር ያስታወሱት ድርጅቱ፣ “ከዚያ በኋላ ደግሞ ጦርነት መጥቷል። ስለዚህ ሱሱ ለመስፋፋቱ ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንያቱም ወጣቶች የሚውሉባቸው ቦታዎች፣ ኢንፍራስትራክቸሮች፣ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች በጦርነት ይወድማሉ” ብሏል።


“ወጣቶች ከትምህርት ቤት ውጪ ሲሆኑ ተስፋ የመቁረጣቸው ሁኔታ እየጨመረ ሲሄድ ለጫት፣ ለሲጋራ፣ ለመጠጥ የሚዳርጋቸው ነገር Automatic ነው የሚሆነው። ጦርነቱ፣ ስራ አጥነቱ አባባሽ ምክንያቶች ናቸው” ብሎ፣ የችግሩ ምንጮች ላይ በማተኮር መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል በማስገንዘብ፣ “ጫት በብዛት የሚመረትባቸው፣ የሚከፋፈልባቸው ቦታዎችን መለየት ያስፈልጋል” ባይ ነው።


“አንዱ ትልቁ መሰራት ያለበት ክልከላ ነው” የሚሉት የድርጅቱ አካል አቶ ሲሳይ ታረቀኝ፣ “ለምሳሌ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ጫት ቤቶች እንዳይከፈቱ፣ ይህን ያህል ርቀት ይሁን ይባላል። ግን እሱ ሲተገበር አናይም” ሲሉ ክፍቱን ጠቁመዋል። 


“የጫት ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው። ጤናን ያናጋል። ምክንያቱም ሱስ አስያዥና ለሰውነታችን ባዕድ ንጥረ ነገር ነው ወደ ሰውነታችን የሚገባው” ያሉት አቶ ሲሳይ፣ ችግሩን ለመቅረፍ በጣም የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 
ጫት ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ቢያስከትልም ለሀገርም ደግሞ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የኤክስፓርት አይነት መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ጫት ይከልከል ቢባል ለአርሶ አደሩም ሆነ እንደ አጠቃላይ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አያስከትልም ወይ? ይህን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?


ይህንኑ ጥያቄ በተመለከተ በሰጠው ሃሳብ እሸት ችልድረን የኤንድ ዩዝ ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን፣ ጫት ለሀገር ከፍተኛ ገቢ እንዳለው ገልጾ፣ በአንድ ጊዜ ምርቱን ማቆም ሳይሆን አርሶ አደሩ የጫት ማሳውን በማንጎ፣ ፓፓያና መሰል አትክልትና ፍራፍሬ እንዲቀይር በማስገነዘብ ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ አቅራቧል።


ለአብነትም በአማራ ክልል ባሕርዳር አካባቢ አርሶ አደሮች የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትሉ የሰብል አይነቶች የጫት ማሳቸውን እንዲቀይሩ የማድረግ ተሞክሮ ሲሰራ እንደቆዬም ተሞክሮውን አስታውሷል።


የሲቪል ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን መንግስት ራሱ፣ በጫት ማምረት፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ ውስጥ ያሉ ሁሉ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተጠይቋል።


የጫትን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳቱንም ማሰብ እንደሚገባ፣ ጫት ለተጠቃሚው አስከፊ ጉዳት እንደሚያስከትል መለፈፍ ብቻ ሳይሆን እንዴት ችግሩ እንደሚቀረፍ የባለድርሻ አካላት ተግባር ተኮር ንግግር እንደሚያስልግ ተገልጿል።
ሰሱኞችን በዘላቂነት ከሱስ እንዲወጡ ሰፊ ስራ መደረግ እንዳለበት፣ የህግ ክልከላዎችን የማበጀት እንደሚያስፈልግ፣ ጫትን ጉዳት መቀነስ የሚቻለው በዚህ አካሄድ መሆኑን የሚመለከት ምክረ ሀሳብ ከዘርፉ ተቋማት ቀርቧል።


የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ ማሞ እንደሚሉት ደግሞ፣ ለማህበረሰቡ የማያቋርጥ፣ በእቅድ የተያዘ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት ይገባል። የሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የአንድ ተቋም ብቻ ልፋት የወጣቱን ከሱስ መዘፈቅ እንደማያድን፣ ሆኖም ሚዲያዎች በአንዳንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁሌም የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘገባ እንዲሰሩ አሳስቧል።


ሚኒስቴሩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ፣ ሆኖም ገና ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ፣ የቅንጅት ሥራ እንደሚያስፈልግ፣ ወደ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደተሰጠ ተመልክቷል። 

በህክምና ከሱስ መላቀቅ ይቻል ይሆን?

ራሱን “እድለኛው” ብሎ የሚጠራው ከገባበት የሱስ ህይወት ከመውጣት ባሻገር “ጉድ ላክ የሱስ ማገገሚያና የስልጠና ማዕከል ግብረ ሰናይ ድርጅት” ለመክፈት መብቃቱን የገለጸው አቶ ዮናታን ሊዮን፣ “ከሱስ ህይወት መውጣት ይቻላል” ሲል በሙሉ ልብ ይመሰክራል።


የድርጅቱ መስራች፣ “በሱስ ምክንያት ደም እስከመትፋት ሁሉ ደርሸ ነበር። ጫት፣ ሲጋራ፣ ሀሽሺ፣ የሀበሻ አረቄ ነበር የምጠቀመው። እነዚህን ካልተጠቀምኩ ሰውነቴ ይንቀጠቀጥ ነበር። ለሞት እደርስ ነበር” ሲል በሱስ የደረሰበትን ጉዳት እንደ ታሪክ ያወሳል።

“ቀኑን ሙሉ የኔ ዳምፔል ብርጭቆ/መጠጥ ነበር። ሳልጠጣ አልውልም ነበር” የሚለው አቶ ዮናታን፣ ከአመታት በኋላ ራሱን በሱስ ጎድቶ ካገኘው በኋላ በሰዎች ጥቆማ አማካኝነት የሱስ ማገገሚያ ተቋማት እንደገባ ገልጿል።


ከሱስ ቁራኝነት ለመውጣት በማገገሚያ ቦታ ጸንቶ መቆየት ወሳኝ እንደሆነ ባስረዳበት አውድ ባለታሪካችን፣ “ግን ወር ከስድስት ቀናት ቆይቼ ወጣሁ። ከስድስት ወር በኋላም አገረሸ። ሱስ ጥንቃቄ የሚፈልግ በሽታ ነው” ሲል አስከፊነቱን አስረድቷል።


“በድጋሚ ገባሁ፣ ተመልሸ ስወጣ አገረሸ፣ ሦስተኛ ገባሁ” ያለው አቶ ዮናታን፣ “በሽታ ነው ሲሉኝ አልሰማም ነበር። ለካ ሱስ በሽታ ነው። ግን መዳን የሚችል፣ የሚያገረሽም በሽታ ነው። ለ22 ዓመታት ነው በዚህ በሽታ ውስጥ የቆየሁት” ሲል ይናገራል።


“በኋላ መዳን በሚችል በሽታ ሰው ለምን ይሞታል? የሚል ራዕይ ያዝኩ” የሚለው አቶ ዮናታን፣ መጨረሻ ላይ ሱስ አቆሞ፣ የማገገሚያ ድርጅቱ አቋቁሞ 351 ሰዎች ከሱስ እንዲያገግሙ ምክንያት መሆኑን በደስታ ገልጿል።

በአማኑኤል የአእምሮ ህሙማን ሆስፒታል የሥነ ልቦና ህክምና ባለሙያው አቶ እንዳለ ማሞ በበኩላቸው፣ ሱስን ታክሞ መዳን እንደሚቻል ገልጸው፣ የሱስ ተጠቂዎች ቁጥር  የሚጨምረውና የሚቀንሰው፣ የህክምና አገልግሎቱን ካለማወቅና አውቆ ከመምጣት ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።


“ቁጥሩ ሲጨምርና ሲቀንስ አገልግሎቱን ከማወቅና ካለማወቅ አንጻር፣ ሱስ ይታከማል ከሚልና ከማይል እይታም አንጸር ይወሰናል። ሌላኛው ደግሞ ወደ ሆስፒታል መጥተው ራሳቸው እንታከማለን ብለው ከማመንና ካለማመን፣ ከመፈለግና ካለመፈለግ ጋርም ይገናኛል” ብለዋል።


“አንዳንዴ ቁጥሩ ከፍ ሲል የሚታከሙ ሰዎች ስለፈለጉ ነው። ቁጥሩ ካልጨመረ አንሶ ሳይሆን ታካሚዎች ወደ ህክምና ያለመምጣት ፍላጎት ስለሌላቸውም ጭምር ነው። ምክንያቱም ሱስ የሚባለው ህመም ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢያውቁም መጥተው መታከም ላይልጉ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።


“በህክምና ከሱስ መውጣት ይቻላል እንዴ? የከበደንኮ ከሱስ ህይወት መውጣት ነው” የሚሉ ወገኖች አሉና እውነትም በህክምና ከሱስ መውጣት ይቻላል? ከሱሱ ለማገገም ምን ያክል ጊዜ ይወስድባቸዋል? ምንስ ማድረግ አለባቸው? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ የህክምና ባለሙያው ተከታዩን መልሰዋል።


“ማገገሙ ሱስኛው እንዳለበት የሱስ ደረጃ ይወሰናል። የሱሱ ደረጃ ያመጣባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ፣ በሱስ የመጣበት ጉዳት ይወስነዋል። ብዙ ሳይጎዳ ቀድሞ የሚመጣ አለ። ረጅም ጊዜ ተጠቅሞ የሚመጣ ሰውም አለ። ሰዎች ከሱስ ለመውጣት በመጀመሪያ ደረጃ ፍላጎትም ሊኖራቸው ይገባል” ሲሉ አስገንዝበል።


“አንድ ሰው የግድ ህክምና ስለተደረገለት ብቻ አይደለም ሱስ የሚያቆመው። የሰውየውን ውሳኔ፣ ቁርጠኝነት፣ ህክሞና ላይ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። ስለዚህ የማገገሚያ ጊዜ ሰዎች እንዳሉበት ሁኔታ ይወሰናል” ነው ያሉት።


“ሌላው እስከ ህይወት ፍፃሜያቸው ድረስ ሜቴይናንስ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች አሉ። ለረጅም ጊዜ በመድኃኒት ክትትል፣ በሥነ ልቦና ድጋፍ የሚቆዩ ታካሚዎች አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በቶሎ የማገገም ሂደት ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ በጊዜ መወሰን ይከብዳለል” ብለዋል፡፡“የሥነ ልቦና እርዳታ እንኳን ቢያስፈልግ ከ3 እስከ 6 ወራት ጊዜ ክትትል ያስፈልጋል። የመድኃኒትም ድጋፍ ልክ እንደዛው። በአንዴ ማገገም አይቻልም። ግን ማገገም ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል።


በዚህ ክፍል ስለሱስ አስከፊነት ከሰፊው በጠባቡ፣ ከትልቁ በትንሹ ምሁራን፣ የሱሱ ሰለባዎች፣ ጥናት፣ ባለድርሻ አካላት ያከፈሉንና መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያካፈልናችሁ ሲሆን፣ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ በሰፊው እስከምንመለስበት መልካም ንባብ ተመኘን። በቸር ሰንብቱ!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 



Eyob Tikuye

Journalist

የዚህ ጹሑፍ አዘጋጅ አዘጋጅ ኢዮብ ትኩዬ ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት ሚዲያና ተግባቦት የተመረቀ ሲሆን፣ በዚሁ ሙያ እያገለገለ ይገኛል።

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.