post-thumb

ኤ.አይ ነው ወይ ?

በዚህ ዘመን የማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም መቻል ወይም ዕድሉን ማግኘት (Able to connect online) ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በዚህ ወቅት መረጃን ከማግኘት በላይ የተጣራና ተዓማኒነት ያለው መረጃን ማግኘቱ ከባድ ነው፡፡

ስልካችንን አልያም ኮምፒውተራችንን መያዝ ወይም ቴሌቭዥን እና ራዲዮ ከፍቶ መከታተል ብቻውን ለመረጃ ቅርብ አያሰኘንም፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሚዲያን ለመከታተል በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያን (social Media) ጤናማ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ክህሎትንና እውቀትን መጨበጥ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነበት ሰዓት ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ፥ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና በተለያየ መልክ መምጣቱ ነው፡፡

ይህ የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከዚህ ቀደም በስፋት እንደሚታየው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳያቆም በሁሉም ዘርፍ በማኅበረሰቡ ውስጥ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ኃብቶችን እየሸረሸረ፤ ሰርቶ ማግኘትን እና ወጥቶ መግባትን ጥያቄ ውስጥ በሚከት መልኩ ሰላማዊ መስተጋብሮችን እያፈረሰ እንደ ሀገር፤ ሀገራዊ ጉዳትን እንደግለሰብ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እየፈጠረ በመሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያን በእውቀት እና በክህሎት መጠቀም ዛሬ ላይ የውዴታ ግዴታ ሆኗል፡፡

በዚህ ዘርፍ:-

 እውቀት ስንል ፦ ከራሳችንን ግላዊ አድሎ (Self biased) ጀምረን ሀሰተኛ መረጃዎች እንዴት፣ በምን፣ በማን፣ ለምን ዓላማ ይሰራጫሉ እና እንዴትስ ይህንን መከላከል ወይም ጉዳቱን መቀነስ እንችላለን ብሎ መማር ማወቅን ሲያመለክት፤

ክህሎት ስንል ፦ እንዴት ደኅንነቱ የተጠበቀ መረጃ ማግኘት እንዳለብን፣ እንዴት ራሳችንን ከሀሰተኛ እና ከተዛቡ መረጃዎች መከላከል እንደምንችል መሰልጠንን ይመለከታል፡፡ 

ይህ በጠቅላላው የሚዲያ እና የዲጂታል እውቀትና ክህሎት (Media and Digital Literacy) ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡

እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የኢንተርኔት አገልግሎት ለዓለም ከተዋወቀ በኋላ ሰዎች እንዴት መረጃን ማግኘት፣ መረዳት እና ማጋራት እንዳለባቸው የሃሳብ ልውውጥ የሚደረግባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

አሁን ላይ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የበለጠ ከጄኔሬቲቭ ኤ.አይ (Generative AI) መፈጠር ጋር ተያይዞ ግን፤ ሌላ ክህሎትና እውቀት አስፈልጓል፡፡ ይህም የኤ.አይ ክህሎትና እውቀት (Literacy) ነው፡፡ የኤ.አይ ክፍሎትና እውቀት፥ ከሚዲያና ዲጂታል ክህሎትና እውቀት ጋር ሊለያይ በማይችል መልኩ፤ በብዙ የተቆራኘ ሆኗል፡፡

እንደ ሀገራችን መደበኛው የእውቀትና ክህሎት (Literacy) ደረጃ እንኳን ከግማሽ ብዙም ፈቀቅ ባላለበት ሁኔታ የሚዲያ እና የዲጂታል አጠቃቀም እውቀትና ክህሎት ክፍተቱ ሰፊ መሆኑ አይደንቅም፡፡

በዚህ ላይ አሁን በፍጥነት እያደገ የመጣው የሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) ዘርፍ ሲታከልበትና እና የኢንተርኔት ተጠቃሚነት (Internet Connectivity) መስፋፋት ሲደመርበት ለህብረተሰባችን እውቀትና ክህሎት ማስጨበጥ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡

የኤ.አይ ክህሎትና(AI) እውቀት መቼ ያስፈልገናል ? . . . አሁን ያስፈልገናል!

ኤ.አይን መሰረት ያደረጉ ሀሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በጹሐፍ ወይም ፎቶ በማቀናበር ይለቀቁ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎች አሁን ላይ በቀላሉ ጹሑፍም ሆነ ተለጣፊ ምስል(Picture) ወይም ተንቀሳቃሽ ምስል(Video) የታገዘ ለማድረግ ቀላል ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ሥርጭቱንና መጠኑን ጨምሮታል፡፡

በኤ.አይ የሚፈጠሩ ይዘቶች ለእይታ ሳቢ እና አጓጊ ሆነው ስለሚፈጠሩም በቀላሉ ሰዎች ጋር የመድረስ እና የማሳመን አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እንዳንዶቹን ይዘቶች መለየት እስከሚከብድ ድረስ ለፍጹም ምስስል የቀረቡ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ስጋቱ ደግሞ በሚፈጠሩት ምስሎችና ቪዲዮች ብቻ ላይ የሚያቆም አይደለም፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት የሚጠቀሟቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት የሚመርጡበት፣ የሚመድቡበትና ተስማሚ ጥቆማዎችን የሚጋሩበትን መንገድ (Algorithms) ዘመናዊ በማድረግ በኤ.አይ የታገዘ በማድረጋቸው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥጥር ከሚደረግበት አሰራር ወደ ልቅ የሆነ ተደራሽነት ያዘነበለ አሰራር በመከተላቸው፤ እንዲሁም የይዘት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ማተኮራቸው ለጤናማ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ራሱን ያቻለ ሥጋት የሚፈጥር ጉዳይ ሆኗል፡፡

ለዚህ ነው የሚድያ እውቀትና ክህሎት (Media Literacy) አሁን ያስፈልገናል ማለታችን! ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄም (Campaign) እንቅስቃሴያችንም ባለፉት ሦስት ወራት 12 ተማሪዎችንና 12 የማኅበረሰብ ራዲዮ ጋዜጠኖችን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ ወደ 20 የሚጠጉ የማኅረሰብ አካላትን ሥልጠና በሰጠንበት ወቅት፥ ኤ.አይን መሰረት ያደረጉ ሀሰተኛ መረጃዎች እየተሰፉፉ መምጣታቸውን በምልከታችን መገንዘብ ተችሏል፡፡

በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄም ቢያንስ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚመለከቷቸውን ይዘቶች ለሰዎች ከማጋራታቸው በፊት ቆም ብለው ኤ.አይ ነው? ወይንስ እውነት ነው? ብለው ለአፍታ እንዲጠይቁ በማድረግ፤ የኤ.አይ ይዘቶችን የሚለዩበትን መሰረታዊ መንገዶችን ለማስጨበጥ ያለመ ነው፡፡

ከህዳር 4 እስከ ህዳር 14 በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ (Campaign) የኤ.አይ ይዘቶችን እንዴት መለየት እንደምንችል ትምህርታዊ ይዘቶችንና ጠቃሚ መረጆች እናጋራለን፡፡ የጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲሁም ይህን የተመለከቱ ልዩ ልዩ አሳታፊ መርኃ-ግብሮችንም አካቷል፡፡ 

ይህም ሰዎች ይዘቶችን እንዲፈትሹ እና ራሳቸውን ኤ.አይን መሰረት ካደረጉ ከሀሰተኛ መረጃዎች ከመታለልና ሰዎችንም በስህተት ከማታለል እንዲቆጠቡ መጠነኛ ግንዛቤ የሚፈጥር ይሆናል ተብሎ ታስቧል፡፡ እርሶም በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ አብረውን በመሳተፍ የበኩሎን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንጠይቃለን፡፡



Concept Hub Ethiopia

Admin

Emerging Voices: A hub for thought leadership and professionalism

Comments

Leave a Comment

Login or register to interact with an article.