Issue 02 | Apr 2025

  • Concept Hub Ethiopia
  • 06 Apr, 2025

Concept Hub | ሀሳብ አለኝ | Magazine | Issue 02

አጭር መልዕክት

‹‹ሐሳብ አለኝ ›› መጽሔታችን ሁለተኛ ዕትም ለእናንተ ለአንባቢያን ስናደርስ ለወደፊት ያለንን ራዕይ እና ተስፋ ጭምር እንዳካፈልናችሁ ይሰማናል፡፡ ዛሬ ገና ሊገነባ እንዳለ ቤት ቁፋሮው እና ጭቃው ሳቢ ባይሆንም፤ ቤቱ ቤት ሆኖ እንዲቆም የቤቱን ንድፍ እያዩ ለፍጻሜው መስራት እንሚገባ ሁሉ÷ ይህም መድረክ ለብዙዎች የሐሳባቸው ማረፊያ እንደሚሆን በማሰብ፤ ዛሬ ምንም እንኳን ጅማሮ ላይ ቢሆንም ራዕያችንን እያሰብን ከመስራት ግን አናቋርጥም፡፡

እንደከዚህ ቀደሙ ዛሬም ደግመን የምንናገረው ሐሳብን በጹሑፍ ማስፈር መቻል ትልቅ ክህሎት ነው፤ የብዙ ነገርም መሰረት ነው፡፡ አብዛኞቻችን በአዕምሯችን የሚመላለሰውን ወይም የተሸለ እውቀት አለን ብለን የምናስበውን ሐሳብ ወደ ጹሑፍ መቀየር ብንችል ብዙ የምናካፍላቸው ታሪኮች፤ እውቀቶችን ልምዶች ከመኖራቸውም በላይ ከሌሎች አማራጮች በተሸለ መልኩ እንድናስብ፤ እንድንመረምር፤ ሐሳባችንን ከማካፈላችን በፊትም በሐሳባችን እና በእኛ መካከል የጥሞና፣ የአስተውሎት፣ የማሰላሰል ሂደቶች እንዲፈጠር እድሉን ይሰጠናል፡፡ 

ማብበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል እንደሚባለው ሁሉ ጥሩ ጸሐፊም ሙሉ ሰው ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ የአንባቢያን ቁጥር ቀነሰ ስንል በተዘዋዋሪ የጸሐፊያኑም መጠን በዚያው ልክ እንደሚሆን፤ የንባብ ባህልን ማዳበር አለብን ስንልም በተመሳሳይ ጸሐፊዎችን ማበረታታት እንዳለብን መገንዘብ መቻል አለብን፡፡ ለዚህ ነው ይህ መድረክ የተፈጠረው፡፡ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ሐሳባቸውን አውጥተው በጹሑፍ እንዲያሳዩ፤ የጹሑፍ ችሎታ ያለቸው ሰዎች ይህንን ችሎታቸውን ማሳየት እንዲችሉ፤ እንዲሁም አንባቢያን ደግሞ እንዲሞግቱና ለውጥ መፍጠር የሚችሉ ሐሳቦች እንዲቀረጹ በማሰብ ነው፡፡ 

በየትኛውም ዘርፍ ያላችሁ ወጣት ባለሞያዎች፣ በልዩነት በጋዜጠኝነት የተመረቃችሁ፣ በትምህርት ላይ ላላችሁ ይህ መድረክ ሐሳብ ወደ ጹሑፍ የሚቀየርበት ብቻ አይደለም፡፡ ራሳችሁን የምታሳዩበት፤ አቅማችሁን የምትገልጹበት፤ ከሌሎች በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ ካሉ ወንድሞች እህቶች ጋር እንዲሁም ባለሞያዎች ጋር የምትተዋወቁበት መድረክ ጭምር ነው፡፡ ይህ መድረክ ሙያዊ መርህን ተከትላችሁ በነጻነት የምትጠቀነሙበት ነው፡፡

አንባቢያንም በየጹሑፎቹ ያሏችሁን አስተያየት በመስጠትና ውይይትንና ትኩረትን በሚያሰፋ መልኩ ተሳትፏችሁ እንዲቀጥል እንጠይቃለን፡፡

መልካም ንባብ !